በአማራ ክልል በሁለት ወራት ውስጥ በተካሄደው የህገ-ወጥ ነዳጅ ቁጥጥር ዘመቻ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ መያዙ ተገለጸ!
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ምርት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከየካቲት ወር/ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገዉ ጥብቅ ክትትልና ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ንቅናቄ ፣ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ከተሞች በህገ-ወጥ ንግድና ዝውውር ላይ የነበረ ነዳጅ (ናፍጣና ቤንዝን) በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁሟል።
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከማኅበረሰቡ በደረሰው ጥቆማና ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዱና ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ሕዝብን የሚያማርሩ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ማክሸፍ መቻሉንም አመላክቷል።
እንደ ክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጻ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የክልሉ የጸጥታ ኃይል በድንገተኛ የኬላና የቤት ውስጥ ፍተሻ 88 ሺህ 40 ሊትር ናፍጣ እና 13 ሺህ 671 ሊትር ቤንዚን በህገ-ወጥ መንገድ ተከዝኖና ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጧል።
14 ሺህ 63 ሊትር በላይ ናፍጣ በህገ-ወጥ መንገድ ሲሸጥ የተገኘ አንድ ማደያ ላይም አገልግሎት እንዳይሰጥ የታሸገ መሆኑን ገልጿል።
በድንገተኛ ፍተሻ በቁጥጥር ሥር የዋለው ይህ ነዳጅ በዋናነት ለህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ስምሪትና ለትላልቅ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀ እና ለችርቻሮ ሽያጭና ለሕገ-ወጥ ትርፍ ተከዝኖ የነበረ መሆኑንም ጠቁሟል።
ይህ መጠነ ሰፊ ክትትል የነዳጅ ምርትን ለግል ጥቅማቸውና ለአጥፊ ተግባራት ለማዋል የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንቅስቃሴ የገታ መሆኑንም ዋና ጠቅላይ መምሪያው አረጋግጧል።
በተለይም ነዳጅን በሰጋቱራ፣ በፍራሽና በሌሎች ቁሳቁሶች በመደበቅ ለማሳለፍ የተሞከሩ የረቀቁ ዘዴዎች በጸጥታ ኃይሉ ንቃትና ጥንቃቄ የተሞላበት ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የክልሉ የጸጥታ ኃይል ህገ-ወጥነትን ለመቆጣጠር ያሳየውን ቁርጠኝነት ያመላክታል ሲልም የክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አመላክቷል ።
ዋና ጠቅላይ መምሪያው የነዳጅ ስርጭቱ ሥርዓት ይዞ ለሕዝብ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲደርስ ለማድረግ የጀመረውን ጥብቅ ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
በሰንሰለቱ ውስጥ የሚሳተፉና ነዳጅን ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች አሳልፈው የሚሰጡ ማደያዎችና ግለሰቦች ላይም የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ለዚህ ስኬታማ ኦፕሬሽን የማኅበረሰቡ ጥቆማና ከፖሊስ ጎን መቆም ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ የገለጸው ዋና ጠቅላይ መምሪያው በቀጣይም ሕዝቡ የዜግነት ድርሻውን በመወጣት መሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን እንዲያጋልጥ ጥሪውን አቅርቧል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
በጀግንነት መጠበቅ!
በሰብዓዊነት ማገልገል!






