ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ የተሰጠ የትንሳኤ በዓል የጸጥታና የጥንቃቄ መግለጫ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ (ፋሲካ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በዓሉ በሰላም፣ በደስታና በታላቅ መንፈሳዊነት እንዲከበር የክልላችን ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል።
የጸጥታ ኃይላችን በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች፣በሃይማኖታዊ ተቋማት፣ በሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችና በኬላዎች ጠንካራ ስምሪት በመውሰድ የ24 ሰዓት የጥበቃና የክትትል ተግባሩን በንቃት እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በዓሉን ስናከብር ከወንጀልና ከአደጋ ነጻ ለመሆን ህብረተሰቡ የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች እንዲያደርግ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ አሳስበዋል፦
1. ከአጭበርባሪዎች መጠንቀቅ፦ በበዓላት ሰሞን የሚስተዋሉ አታላዮችንና አጭበርባሪዎችን በመለየት፣ ግብይት ሲፈጽሙ በሕጋዊ የገበያ ማዕከላት ብቻ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን።
2.የእንስሳት ግብይት፦ ከምንጩ ያልታወቁና የተሰረቁ እንስሳትን ከመግዛት በመቆጠብ ራስዎን ከሕግ ተጠያቂነት ይጠብቁ።
3.ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች፦ በግብይት ወቅት ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለይተው እንዲጠነቀቁና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙ በአቅራቢያዎ ለሚገኝ ፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ እናሳስባለን።
4.ቤትና ንብረትን መጠበቅ፦ ለጸሎትም ሆነ ለተለያዩ የበዓል ፕሮግራሞች ከቤት በሚወጡበት ወቅት ቤቶቻችሁ በአስተማማኝ ሁኔታ መቆለፋቸውንና ጥበቃ መኖሩን ያረጋግጡ።
5.የትራፊክ ደህንነት:- አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር ለከፋ የሕይወትና የንብረት አደጋ ስለሚያጋልጥ፣ አሽከርካሪዎች ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የትራፊክ ፍሰቱ ስለሚጨምር፣ ከፍጥነት በላይ በሚያሽከረክሩ፣ ከመጠን በላይ በሚጭኑና ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥርና የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።
6.ለእሳት አደጋ ጥንቃቄ ማድረግ፦ የበዓል ምግብ ዝግጅት በሚከናወንበት ወቅት የእሳት አደጋ እንዳይከሰት የኤሌክትሪክና ሌሎች የማብሰያ መሣሪያዎችን (ጧፍና ሻማን ጨምሮ) በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ እናሳስባለን።
8.ህገ-ወጥ ንግድንና አጠራጣሪ ነገሮችን ማሳወቅ ፦ በበዓሉ ስም አጋጣሚውን በመጠቀም የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ፣ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና የህዝቡን ሰላም ለማወክ የሚሞክሩ አካላት ላይ ፖሊስ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ ያደርጋል።
የወንጀል መከላከል ሥራ ስኬታማ የሚሆነው በማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎና የተቀናጀ ጥረት በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅና ማንኛውንም ለየት ያለ አጠራጣሪ ሁኔታ ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ ኃይል ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የጸጥታ ኃይላችን በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ ማንኛውንም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
ሰላም የሁላችንም መሰረት በመሆኑ፣ ህዝባችን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ተግባራዊ ባደረገው የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app ) በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የዞን ፖሊስ መምሪዎች ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ስማርት ስልካቸውን በጠቀም መረጃዎችን ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉና ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ አሳስበዋል።
በድጋሚ መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ
መጋቢት 2018 ዓ.ም

