“ፖሊስ በምርጫ ወቅት የህዝብን ደህንነትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“ፖሊስ በምርጫ ወቅት የህዝብን ደህንነትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስን ሚና እና ሙያዊ ስነ-ምግባር ለማጠናከር በ5 ክላስተሮች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ፖሊስ በምርጫ ወቅት የህዝብን ደህንነትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

ሰራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በመሆን፣ በታማኝነትና በገለልተኝነት ህዝባዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

መራጮች ያለምንም ስጋትና ፍራቻ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ወጥተው ድምፃቸውን እንዲሰጡ ምቹና ሰላማዊ ከባቢ መፍጠር፤

የምርጫ ጣቢያዎችንና ቁሳቁሶችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ፤

ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ያለውን አጠቃላይ ሂደት በንቃት መከታተል፣ መቆጣጠርና የጸጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ማስጠበቅ፤

ማንኛውንም አይነት ሁከትና ብጥብጥ አስቀድሞ በመከላከል፣ ሂደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻን መወጣት ይገባል ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራሉ በምርጫው ሂደት የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው አስታውቀዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የተሰጠው ስልጠና በምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ስጋቶችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻልና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ስለመስራት ትልቅ ግንዛቤ የጨበጡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ፖሊስ የህግ አስከባሪነቱን ሚና ሲወጣ ሰብአዊ መብቶችን ባከበረና ሙያዊ ስነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ መሆን እንዳለበት መረዳታቸውን ጠቁመዋል።

ሰራዊቱ የተጣለበትን አደራ ለመወጣትና ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ በቁርጠኝነት ዝግጁ መሆኑንም ተሳታፊዎቹ አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top