“የመደመር መንግስት የኢትዮጵያ ፖሊስ በሚሰጠው አገልግሎት ታማኝም አሳማኝም መሆን አለበት ብሎ ያምናል!” – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

“የመደመር መንግስት የኢትዮጵያ ፖሊስ በሚሰጠው አገልግሎት ታማኝም አሳማኝም መሆን አለበት ብሎ ያምናል!” – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የኢትዮጵያ ፖሊስ በስራውና በሚሰጠው አገልግሎት ለህዝብ ታማኝና አሳማኝ መሆን እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ዛሬ “ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል መካሄድ በጀመረው 20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በንግግራቸውም የፖሊስ ተቋምን ለማዘመን እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው የፖሊስ ሪፎርም፤ ተቋሙ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በዕውቀት እንዲዳብር በማድረግ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምሳሌ መሆን የሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኝ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ፖሊሶች ለሕገ-መንግስቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ታማኝ ሊሆኑ እንደሚገባ ያሳሰቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ” የሚለውን መርህ በመያዝ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጥፋት ኃይሎች በሀገሪቱና በሕዝብ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት የፖሊስ ኃይሉ በአንድነት በመቆምና መስዋዕትነት በመክፈል ማክሸፉ የሁሉንም ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገርን እድገት የማይፈልጉ ኃይሎችን ሴራ በንቃት የማክሸፍ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም በመጪው ግንቦት የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ሀገሪቱ የምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፍ ሁነቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ፖሊስ የላቀ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም የፖሊስ አመራሮችና የሠራዊቱ አባላት ራሳቸውን በዕውቀት፣ በታማኝነትና በሕዝብ አገልጋይነት ስነ-ልቦና ለላቀ ተልዕኮ ዝግጁ እንዲያደርጉ አደራ በማለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል መካሄድ በጀመረው 20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እየተሳተፈ ይገኛል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top