7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ ፖሊስ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን ገለጸ።
መጪው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
ምርጫው ፍትሐዊ፣ ታዓማኒ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ምርጫወው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ሚናው የጎላ በመሆኑ ያብራሩት ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሹ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን አካላትን እኩይ ሴራ በማምከንና ማህበረሰቡ የሚፈልገው እንዲመርጥ ዋስትና መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ሂደቱን ለማስተጓጎል የሚጥሩ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን አካላት መስተዋላቸውን የጠቆሙት የፖሊስ አዛዡ አክለው ተናግረዋል።
ህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድኑ ለውጭ እና ለውስጥ ጠላቶቻችን የጥፋት አጀንዳ ማስፈፀሚያ በመሆን ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ላልተገባ ግጭትና ውድመት መዳረጉ ሳያንስ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የማህበረሰባችንን የመምረጥ እና የመመረጥ ዲሞክራሲያዊ መብትን በመጣስና የህዝብን ነፃነት በመጋፋት እያደረገ ያለው እኩይ ተግባር ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የክልላችን ማህበረሰብ ያለምንም የፀጥታ ስጋትና ያለማንም ተፅዕኖ የሚፈልገውንና የሚጠቅመውን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት መምረጥ እንዲችል የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ሰርጎ በመግባት የሽብር ተግባር ለመፈጸም የሚሞክሩ ፅንፈኛ ታጣቂ ኃይሎችን እና የተለያዩ ስጋቶችን የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ወስዶ ቅድመ ዝግጅት ያደረገ መሆኑንም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

