በሞጃና ወደራ ወረዳ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ህገ-ወጥ ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ

በሞጃና ወደራ ወረዳ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ህገ-ወጥ ቤንዚን በቁጥጥር ስር ዋለ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ መነሻውን ከደብረ ብርሃን ከተማ በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሰላ ድንጋይ ከተማ ሊገባ የነበረ 352 ሊትር ቤንዚን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

የወረዳው ፖሊስ ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን ደረጄ ወርቁ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ነዳጁን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ የነበረው አሁን ላይ ያለውን የነዳጅ እጥረት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምና ከፍ ባለ ዋጋ በመሸጥ ማኅበረሰቡን ለመበዝበዝ በማሰብ ነው ብለዋል።

ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማና ፖሊስ ባደረገው ክትትል ነዳጁ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለውም በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር የሚታየውን የነዳጅ እጥረት ችግር ተገን በማድረግ አንዳንድ ስግብግብ ግለሰቦች ነዳጅን በመከዘንና በእጥፍ ዋጋ በመሸጥ የሕዝቡን እንግልት እያባባሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ይህንን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመግታት ፖሊስ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በቀንና በሌሊት እያደረገ ያለው ጠንካራ የፍተሻና የክትትል ሥራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርንና መከዘንን ለመከላከል ሕብረተሰቡ እያደረገ ያለው የተለመደ ትብብር የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው ወደፊትም መሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሲያጋጥሙ መረጃ በመስጠትና ከፖሊስ ጎን በመቆም የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያም በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና የፍተሻ ኬላዎች ላይ መሰል ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር ዝግጁነቱን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top