በእንጅባራ ከተማ በሰጋቱራ ተሸፍኖ ሲጓጓዝ የነበረ ህገ-ወጥ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እንጅባራ ከተማ መውጫ ኬላ ላይ በተደረገ ጥብቅ ፍተሻ በረቀቀ ዘዴ ተደብቆ ሊወጣ የነበረ 40 በርሚል ህገ-ወጥ ነዳጅ ከጭነት ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው ፖሊስ አስታወቀ።
መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም 1፡30 ሰዓት ገደማ ከእንጅባራ ወደ ቻግኒ ከተማ ሊወጣ የነበረው የሰሌዳ ቁጥሩ አአ 17124 ኮድ 3 የሆነ ኤፍ ኤስ አር (FSR) የጭነት መኪና 40 በርሚል ነዳጅ ከጫነ በኋላ እንዳይታይ በማዳበሪያ የታሸገ ሰጋቱራ በላዩ ላይ በመደርደር ለመሸፈን ሞክሮ ነበር።
ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ድርጊታቸው በጸጥታ ሃይሉ እንዳይታወቅ ለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ይሁን እንጂ የፖሊስ አባላት ከህብረተሰቡ ባገኘው ጥቆማ መነሻነት ባሳዩት ከፍተኛ የንቃትና የፍተሻ ብቃት ተሽከርካሪው በቻግኒ መውጫ ኬላ ላይ ሊያዝ ችሏል።
የእንጅባራ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ታከለ ብርሀን እንደገለጹት የተሽከርካሪው አሽከርካሪ ለጊዜው ከአካባቢው የተሰወረ ቢሆንም ረዳቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ፖሊስ የአሽከርካሪውን አድራሻ ለመለየትና በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትሉን ቀጥሏል ብለዋል።
እንደ ዋና ሳጅን ታከለ ብርሀን ገለጻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ እጥረት የሚታይበትና መንግስት ስርጭቱን ለማስተካከል እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራት በህዝብ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
ይህንን የተረዱት የጸጥታ አካላት በኬላዎች ላይ የሚያደርጉትን ፍተሻ አጥብቀው በመቀጠላቸውና ከህዝቡ ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከራቸው ድሉ ሊመዘገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የእንጅባራ ከተማ ፖሊስ የህዝቡን የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችንና አዘዋዋሪዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥቆማና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የጸጥታ ሃይሉም መሰል የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለመግታት በቀንና በሌሊት በትጋት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።


