በደቡብ ወሎ ዞን በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ
በደቡብ ወሎ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተከናወነ ሰፊ የሙስና ወንጀል ምርመራ በስልጣን አላግባብ መገልገል እና በእምነት ማጉደል ወንጀል የተከሰሱ በርካታ ግለሰቦች በከባድ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አሳምነው ሙላት እንደገለጹት ፖሊስ በዞኑ ውስጥ የመንግስትንና የህዝብን ሀብት ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ትኩረት በማድረግ ባከናወነው ጥብቅ የምርመራ ስራ ውጤት ተመዝግቧል።
የህዝብ አደራን ወደ ጎን በመተው የሀገርን ሀብት ለግል ጥቅም ማዋል የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ ያስከትላል ያሉት ኮማንደሩ የተላለፉት ውሳኔዎች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኩታበር ወረዳ ማዘጋጃ ቤት የስራ ሀላፊዎች በስልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል ተከሰው የካቲት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሚከተለው ከፍተኛ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፦
አቶ አሊ ከበደ የቀድሞ የማዘጋጃ ቤት ሀላፊ በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ1,000 ብር ቅጣት
አቶ ሙህድን አሊ ምክትል ሀላፊ በ4 ዓመት እስራት እና በ2,000 ብር ቅጣት
አቶ አቦል አሸብር በ4 ዓመት ከ5 ወር እስራትና በ2,000 ብር ቅጣት
አቶ ሙሉጌታ በሪሁን በ5 ዓመት እስራትና በ2,000 ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
እነ ኑረዲን መሀመድ አምስት የማናጅመንት አባላት በሌሉበት በተካሄደ ክርክር እያንዳንዳቸው በ5 ዓመት ፅኑ እስራትና በ5,000 ብር ቅጣት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ተከሳሾቹ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው በደሴ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ አዛዡ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ የምርመራ መዝገብ ከባድ ቅጣትከተላለፈባቸው ግለሰቦች መካከልም:-
ኢ/ር ምህረት አያሌው የአድማ መከላከል ሻምበል አዛዥ የነበረ በከባድ የእምነት ማጉደልና በስልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል ተከሶ በሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ9 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል።
እንድሪስ ይመር አሊ የመነሀሪያ የዕለት ገንዘብ ሰብሳቢ የነበረ ከ950 ሺህ ብር በላይ በኦዲት በመጥፋቱ በ5 ዓመት ከ10 ወር ፅኑ እስራት እና በ5,000 ብር ቅጣት ተቀጥቷል።
ሰይድ ሀሰን ሁሴን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ የነበረ የደንበኞችን 5 ሚሊዮን 150 ሺህ ብር በመውሰዱ በ5 ዓመት ከ4 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል።
ኮማንደር አሳምነው ሙላት አክለውም ፖሊስ ሙስናን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን እያካሄደ ያለው ጥብቅ ክትትልና ምርመራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዞኑ ፖሊስ የህዝብን ሀብት ከዘራፊዎች ለመከላከል በማንኛውም የኃላፊነት እርከን ላይ በሚገኙ አካላት ላይ ጠንከር ያለ ምርመራ እያደረገ መሆኑንና ህብረተሰቡም ለዚህ ስኬት ከፖሊስ ጎን በመቆም ጥቆማዎችን በመስጠት ትብብሩን እንዲቀጥል ኮማንደር አሳምነው ሙላት ጥሪ አቅርበዋል።

