በጎንደር ከተማ በፍቅረኛው ላይ ዘግናኝ ግድያና ዝርፊያ የፈጸመው ግለሰብ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ
በጎንደር ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኘው ማራኪ ክፍለ ከተማ፣ አንዲት ወጣት ላይ አሰቃቂ የግድያና የዝርፊያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
ተከሳሽ ብሩክ (ሰለሞን) ደጀን ሲሳይ የተባለው ግለሰብ፣ ሟች ጥጋብ (እናንየ) ሙላትን “የፍቅር ጓደኛዬ ትሆኛለሽ” በሚል አግባብቶ ይዟት ከቆየ በኋላ፣ በባንክ ያላትን ገንዘብና የያዘችውን ስልክ ለመውሰድ እቅድ ያወጣል።
ግለሰቡ ወንጀሉን ለመፈጸም እንዲመቸው “ባህር ዳር የታመመ ቤተሰብ ስላለ እንጠይቅ” በሚል ሰበብ ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከቤቷ ይዟት ይወጣል።
ለሁለት ቀናት ያህል ሁኔታዎች እስኪመቻቹለት ድረስ በተለያዩ ሆቴሎች ሲያዟዙራት ቆይቶ፣ በሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 11 ሰዓት ገደማ ‘ቤተክርስቲያን ተሳልመን እንመለስ’ በሚል ሟችን ቀስቅሶ ወደ አቡነ ሃራ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ከወሰዳት በኋላ፣ መንገድ ላይ ወደሚገኝ ጫካ አስገብቶ በፌሮ ብረት ጭንቅላቷን በተደጋጋሚ በመምታት በአሰቃቂ ሁኔታ
ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።
ተከሳሹ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ የሟችን የኢንፊኒክስ (Infinix) ሞባይል ስልክ እና በባንክ አካውንቷ የነበረን 465,214 ብር ወደ ተለያዩ ሰዎች በማስተላለፍ ወስዷል።
ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘትም በሟች ስልክ ለወንድሟ ‘ፀበል ቦታ ነኝ፣ ብር ስለቸገረኝ ላኩልኝ’ በሚል የሐሰት አጭር መልዕክት በመላክ 86,000 ብር ተቀብሏል።
የሟች ቤተሰቦች በሁኔታው ተጠርጥረው በመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ምርመራ ተጀምሮ ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የጎንደር ከተማ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጠናክሮ ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ አቅርቧል።
ዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን መዝገብ መርምሮ ክስ የመሰረተ ሲሆን፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበረው የክርክር ሂደት ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በመጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ግለሰቡን በ 25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።


