በባለቤቱና በአንድ ዓመት ሕፃን ልጁ ላይ ዘግናኝ ግድያ የፈጸመው ግለሰብ ጽኑ እስራት ተቀጣ

በባለቤቱና በአንድ ዓመት ሕፃን ልጁ ላይ ዘግናኝ ግድያ የፈጸመው ግለሰብ ጽኑ እስራት ተቀጣ

በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ባለቤቱንና ገና የአንድ ዓመት እድሜ የነበረውን ሕፃን ልጁን በ25 ጥይቶች ደብድቦ በመግደል የተከሰሰው ግለሰብ፣ በጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አለህኝ አለባቸው እንደገለጹት፤ ይናገር ደመላሽ ሁኘኛው የተባለው ተከሳሽ የግል ታጣቂ የነበረ ሲሆን፣ ወንጀሉን የፈጸመው ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ገደማ በፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 01 (ሰፈር 3) በተባለ አካባቢ ነው።

ድርጊቱ የተከሰተው በውሃ ቅዳና ልብስ እጠቢ በሚል ምክንያት በተነሳ አነስተኛ አለመግባባት እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ኮማንደር አለህኝ አለባቸው፤ ተከሳሹ በእጁ በነበረ ታጣፊ ክላሽንኮቭ መሣሪያ 25 ጥይቶችን በመተኮስ ባለቤቱን እና በእቅፏ የነበረውን የ1 ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ሕይወት ማጥፋቱን አስረድተዋል።

እንደ ምክትል ኮማንደር አለህኝ አለባቸው ገለጻ ፤ተከሳሹ ከዚህ ቀደምም በባለቤቱ ላይ ተደጋጋሚ ድብደባና አካላዊ ጥቃት ያደርስ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ተከሳሹን በቁጥጥር ሥር በማዋል፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በጥራት አደራጅቶ ለምዕራብ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ ማቅረቡን ኃላፊው ገልጸዋል።

የዞኑ ፍትህ መምሪያ የመደበኛ ወንጀል የሥራ ሂደት ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ፣ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1)(ሀ) መሠረት በከባድ ሰው ግድያ ወንጀል ሁለት የክስ መዝገቦችን በመመሥረት ጉዳዩን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።

ተከሳሹ በችሎት ቀርቦ የተከሰሰበትን ድርጊት በመካድ የተከራከረ ቢሆንም፣ ዐቃቤ ሕግ ባቀረባቸው ጠንካራ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ወንጀሉ መፈጸሙን በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በሁለቱም ክሶች ላይ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር።

ተከሳሹ ያቀረባቸው የመከላከያ ምስክሮች ግን የዐቃቤ ሕግን ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ በሁለቱም ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህ መሰረትም ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ባቀረቡት ጠንካራ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ጥፋተኝነቱ በመረጋገጡ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም በዋለው ችሎት ግለሰቡ እጅ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ምክትል ኮማንደር አለህኝ አለባቸው አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top