በኢትዮጵያ እና በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ በሙሉ ሰላም መጠናቀቁ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ እና በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በባህር ዳር አለምዓቀፍ ስታዲየም የተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ በሙሉ ሰላምና በጥሩ ስፖርታዊ ጨዋነት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ ገለጹ።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ እንዳስታወቁት ጨዋታው በሰላም እና በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ ከተዘጋጀው አጠቃላይ የፀጥታ ማስከበር ዕቅድ ጀምሮ በቅንጅት ሲሰሩ የነበሩ ሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ኃይል ባደረጉት የተቀናጀና ውጤታማ ሥራ ጨዋታው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም የባህር ዳር ከተማ እና የአካባቢው ወጣቶችና መላው ማህበረሰብ ያሳዩት ከፍተኛ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል፣ የስፖርት ፍቅር እና የፀጥታ አካላትን በመተባበር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ላሳዩት መልካም ትብብርና የሰለጠነ ስፖርታዊ ጨዋነት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።




