“ሰላምና ፍቅር የነገሠበት የደመራና የመስቀል በዓል ይሁንልን!” ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለክልሉ መደበኛና አድማ መከላከል ፖሊስ፣ ለሚሊሻ፣ ለሰላም ማስከበር አባላት እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ2019 ዓ.ም የደመራና የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ በመልዕክታቸው የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በጽናትና በቆራጥነት በማገልገል ላይ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዓሉ የፍቅር፣ የደስታና የመደጋገፍ እንዲሆን መልካም የበዓል ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም የመስቀል በዓል የፍቅር፣ የይቅርታና የእርቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴታችን መሆኑን ጠቅሰው፤ የፀጥታ አካላት የሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት ለሀገራችንና ለሕዝባችን ዘላቂ ሰላምን፣ እውነተኛ ወንድማማችነትንና እድገትን እንደሚያበስር ሙሉ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በየግንባሩና በየአካባቢው ሌት ከቀን ሳያቋርጡ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሰላም ሲሉ የፀጥታ አባላቱ የሚከፍሉት ውድ መስዋዕትነትና የሚያሳዩት ጽናት በታሪክ ማህደር ወርቃማ ስፍራ የሚሰጠውና የሚዘከር መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በመጨረሻም በዓሉ ሲከበር እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ህብረታችንን በማጠናከርና የሕዝባችንን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ጥሪ አቅርበዋል።

