የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የምስጋናና የሽኝት መርሃ ግብር አካሄዱ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዘጋጅነት በቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የሽኝት እና የምስጋና ፕሮግራም በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ አዛዥ ክልሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በገጠሙት ጊዜ ሁሉ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግና ኃላፊነታቸውን በብቃት በመወጣት የጎላ ሚና እንደተጫወቱ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አክለውም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም (ዶ/ር) ወደ ክልሉ መጥተው ለማገልገል በነበራቸው ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነት የተቋሙን የፖሊስ ሪፎርም ውጤታማ ማድረግ መቻላቸውን ጠቁመዋል።
ተቋሙን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግና ምቹ እንዲሁም ፅዱ የአሰራር አካባቢን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ስራ መስራታቸውን፣ ፖሊስ ዘመናዊ ህንፃ ባለቤት እንዲሆንና የውስጥ ቁሳቁሶችና ማቴሪያሎች እንዲሟሉ ማድረጋቸውን፣ ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር የነበረውን ቅንጅታዊ አሰራር እና ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገራቸውን አብራርተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) የክልሉ መንግሥት የላቀ ምስጋና የሚያቀርብላቸው መሆኑን ገልጸው፤ በፌደራል ተቋማት በሚያደርጉት የስራ እንቅስቃሴም ቢሆን የክልሉን የፀጥታና የልማት ስራዎች መደገፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱም የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)ባደረጉት ንግግር በቆይታቸው ወቅት ለተደረገላቸው የህዝብና የመንግሥት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ የተሰሩ ስራዎችን ለህዝብ እና ለሰራዊቱ በማሳወቅ ያደረጉት ሚና የጎላ ነበር ሲሉ አክለዋል።
ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ በነበራቸው ቆይታ ሙያዊ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ሳያቆጥቡ ማበርከታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም ቢሆን ለክልሉ ሰላም የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በተያያዘም ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዝግጅቱ ላይ ለተገኙት ለሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ሲናገሩ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ ቀደም ሲል ክልሉን በመደገፍና በማስተባበር ትልቅ ኃላፊነት የተወጡ ከፍተኛ አመራር ናቸው ብለዋል።
አሁን ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሆነው በመመደባቸው የተጣለባቸውን ሀገራዊ አደራ በብቃት እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተለይም ብቁ የፖሊስ አመራር እንዲፈጠር ጠንክረው እንደሚሰሩና በክልሉ የህግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ የማስቻል ስራ እንደሚሰሩ ያላቸውን ጽኑ እምነት አብራርተዋል።



















