“የሕዝብን የሰላምና ደኅንነት ፍላጎት ለማሳካት በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል!” ዶ/ር አማኑኤል ፈረደ
የአማራ ክልል የአስተዳደር ክላስተር ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን፣ በክልሉ የተመዘገቡ አዎንታዊ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በሰፊው ተገምግመዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር አማኑኤል ፈረደ በመድረኩ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር በተለያዩ ፈተናዎች እና ከባድ የሥራ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ለክልሉ ሰላም፣ ደህንነት፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር መረጋገጥ ቀን ከሌት በመትጋት የከበረ ዋጋ እየከፈሉ ላሉ የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
ዶ/ር አማኑኤል አክለውም “የሰላም፣ የደህንነትና የማህበራዊ ጉዳዮችን በትክክል በመምራት እና ትኩረት ሰጥተን በመስራት የህዝብን የሰላም እና የደኅንነት ፍላጎት ማሳካት ያስፈልጋል” ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር አማኑኤል ገለጻ የሕዝቡን አቅምና ፍላጎት በጥልቀት በመገንዘብ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር የስራ ባህል ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በበኩላቸው በፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርምና በፀጥታ ኃይሎች ዝግጁነት ዙሪያ ማጠቃለያ ሰጥተዋል።
የፖሊስ ሰራዊት አባላት ለቀጣይ ተልዕኮ በብቃት እንዲዘጋጁ መደረጉን፣ በስነ-ምግባር፣ በፅናትና በቆራጥነት በኩል አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የተመዘገቡ አዎንታዊ የጸጥታ እና ህግ የማስከበር ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከፌደራል ፀጥታ ኃይሎች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር በየደረጃው እያደገ መምጣቱንና በሚፈጠሩ ጥፋቶች ላይም ተከታትሎ እርምጃ የመውሰድ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ አረጋግጠዋል።
እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በክልሉ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታዎች እንዲሁም በህዝብ ተሳትፎ ዙሪያ ባደረጉት ንግግር የህዝቡን አመኔታና ድጋፍ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ለፀጥታ ኃይሉ የታመነ የመረጃ ምንጭ በመሆን የጠላትን እንቅስቃሴና ሴራ አስቀድሞ በመጠቆም ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት እጃቸውን እንዲሰጡና የሥራ እድል እንዲመቻችላቸው የተደረገው እንቅስቃሴ አዎንታዊ ውጤት ማምጣቱን አስረድተዋል።
የሚዲያ ስራችንን ወሳኝ ስራዎችን ከማሳለጥ፣ ለተቋሙ መጎልበትና ለገፅታ ግንባታ እንደ ትልቅ መሳሪያ አድርገን ተጠቅመንበታል፤ ሆኖም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ አልደረሰም፣ በማለት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በጥንካሬ የመመከት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ተወያዮች እነደገለጹት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ የውጭ ኃይሎችን እና የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን ሴራ አውቆ በመመከት በኩል በርካታ መስዋዕትነት መከፈሉን አንስተዋል።
ቀሪ ቀበሌዎችን ከፅንፈኛ ኃይሎች ነፃ ከማድረግ ባሻገር የልማትና የመልካም አስተዳደር አገልግሎቶችን በፍጥነት የመተካት ስራ መስራት እንደሚገባ ተወያዮች አክለው ገልጸዋል።
በመጨረሻም የፀጥታ መዋቅሩ የማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ መረጃዎችን በፍጥነት የሚከታተል፣ የሚያስተባብልና እውነተኛ መረጃ ለህዝብ የሚያደርስ የተጠናከረ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ስትራቴጂ መተግበር፤
በየደረጃው በሚፈጸሙ ጥፋቶችና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ያለአድሎ የተካሄደ የህግ ማስከበር ስራን በማጠናከር የተጠያቂነት አሰራርን ማስፈን፤
ሰላማዊ መንገድን መርጠው እጃቸውን የሚሰጡ የታጣቂ ቡድን አባላትን ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል፣ የማቋቋምና የሥራ ዕድል የመፍጠር ስራን አጠናክሮ መቀጠል፤
ከፅንፈኛ ኃይሎች ነፃ በወጡ አካባቢዎች የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የልማት ስራዎች ሳይዘገዩ ወዲያውኑ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ማድረግ፤
ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ ስጋቶችንና የጠላት ሴራዎችን አስቀድሞ ለማክሸፍ የመረጃ መዋቅሩንና የመረጃ አሰባሰብን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀሞጧል።



















