የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያን ለማጠናከር ያለመ የውይይት መድረክ አካሄደ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ከህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ አመራሮችና አባላት ጋር በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስና በአቅም ግንባታ ጉዳዮች ላይ የተኮረተ ሰፊ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ለተነሱት ተቋማዊ አሰራር፣ የግብአትና የአቅም ግንባታ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ለተቋምና ለሀገር ግንባታ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ አመራርና አባላት በተቋማዊ አሰራር፣ በግብአት አቅርቦትና በአቅም ግንባታ ዙሪያ ሀሳብና አስተያየቶቻቸውን አቅርበዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማን ጨምሮ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ፣ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ እና ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ሰራዊቱ በስራ ገበታው ሊተገብራቸው የሚገቡ ዋና ዋና የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ፕሮፌሽናሊዝምን ተቋማዊ እሴቶችንና ዲስፕሊንን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ በመሆን የሀገርና ህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ፣ ለሀገርና ተቋም እድገት በቁርጠኝነት መስራትና ለላቀ ውጤት መትጋት፣ የፖሊስን በጎ ስራዎችና እውነታዎች ለህዝብ በትክክል ማዳረስ ይገባል ሲሉ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ሰራዊቱ በስራ ገበታቸው ሊተገብሯቸው የሚገቡ ዋና ዋና የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ውይይቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያን አሰራር ዘመናዊ ለማድረግና የሚታዩ የግብአትና የሰው ኃይል ክፍተቶችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።















