የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ በደብረ ብርሃን ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የፖሊስ ‘ጀግኖች ማዕከል’ የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ እያሌው እና ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አያልነህ ተስፋዬን ጨምሮ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ አመራሮች ተገኝተዋል።
ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ማዕከሉ በፍጥነትና በጥራት ተጠናቆ ለሰራዊቱ አገልግሎት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ከግንባታው ጉብኝት ጎን ለጎን ከአድማ መከላከል ሻለቆችና ከአካባቢው አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ሰራዊቱ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ታማኝ በመሆን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥና የተጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም በተግባር እንዲተረጉም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ለፖሊስ ተቋሙና ለሙያው የማይመጥኑ አሰራሮችና ድርጊቶች በአፋጣኝ እንዲወገዱ ያሳሰቡት ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ጉብኝቱ የሰራዊቱን ዝግጁነት ለመመልከትና ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓት ለመሰብሰብ መሆኑን ገልጸዋል።







