“ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዟችን ስኬት የሚወሰነው ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ስንችል ነው”

“ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዟችን ስኬት የሚወሰነው ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ስንችል ነው”

“በጀግንነት መጠበቅ፣ በሰብዓዊነት ማገልገል” በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ ቀናት ሥልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የደጀን ኃይል የፀጥታ አባላት በደሴ ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተመርቀዋል።

ለተከታታይ ቀናት የተሰጠው ሥልጠና የፀጥታ አባላቱ አካባቢያቸውን ከማንኛውም ዓይነት የጸጥታ ሥጋት የመጠበቅ ብቃታቸውን ከማሳደጉም በላይ፣ ህብረተሰቡን በቅንነት እና በሰብዓዊነት የማገልገል ቁርጠኝነታቸውን የሚያጠናክር ነው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙዔል ሞላልኝ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ አባላት የተጣለባቸውን አደራ እና ህዝባዊ ሃላፊነት በከፍተኛ የዲሲፕሊን መንፈስ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከንቲባው አክለውም የደጀን ኃይሉ የተጣለባቸውን አገር የማዳንና ሰላም የማስበር ታሪካዊ አደራ በሚጠበቅባቸው ወታደራዊ ስነ-ምግባር፣ ጀግንነትና ህዝባዊ ሰብዓዊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) ተመራቂ የፀጥታ አባላት የሀገርን ሰላም፣ ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት ለማደፍረስ ከውጭ ባዳ ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ የውስጥ ባንዳዎችን እኩይ አላማ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ማክሸፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ አባላት ህግና ስርዓትን በማስከበር፣ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ከማንኛውም የወንጀል ስጋት በመጠበቅ ረገድ የድርሻቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አክለውም ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል እና ከአጋር ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመከላከያ ሰራዊት የ11ኛ ዕዝ ም/አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎች የወሰዱትን ሥልጠና በመጠቀም የቀጣናውን ብሎም የክልሉን እና የሀገርን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ ሕዝቡ ወደተሟላ ሰላም እንዲሸጋገር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የደሴ ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ በበኩላቸው ተመራቂዎች በቆይታቸው ተገቢውን ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ የሚያደርጉ፣ ወቅታዊ ሁኔታውን በሚገባ እንዲረዱ የተደረገበትና በቀጣይ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ በሚገባ እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል የአመለካከትና የተግባር አንድነት እንዲፈጥሩ ተደርጓል ብለዋል።

ተመራቂ የፀጥታ አባላቱም በበኩላቸው፣ በሰለጠኑበት ሙያ እና ባገኙት እውቀት መሰረት የከተማዋንና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም ህብረተሰቡን በታማኝነትና በሰብዓዊነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ ሥልጠና አባላቱ የጠላትን ሴራ በንቃት የመከታተል፣ የማክሸፍና ህዝባዊ ደህንነትን በፅናት የመጠበቅ ብቃታቸውን ይበልጥ ያጎለበተ መሆኑ ተመላክቷል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top