የሰላም ጋሻው 29ነኛ ሻለቃ በደብረብርሃን እና አካባቢው!!
የሰላም ጋሻው 29ነኛ ሻለቃ በሰሜን ሸዋ የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥና የጥፋት ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ29ነኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሙሃባው አብርሃም እንደገለጹት ሰራዊቱ በደብረብርሃን እና አካባቢው የተጣለባቸውን ወታደራዊና ፖሊሳዊ ግዳጅ በላቀ የሙያዊ ስነ-ምግባርና በጽኑ ሀገራዊ ፍቅር እየተወጡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የ29ነኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቅርቡ የተካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በፍጹም ሰላምና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ታሪካዊ ሀላፊነቱን መወጣቱንም አክለዋል።
እንደ 29ነኛ ሻለቃ አዛዥ ኮማንደር ሙሃባው ገለጻ ሻለቃው የተሰጡትን ክልላዊና ሀገራዊ ግዳጆች በብቃትና በስኬት እየተወጣ ይገኛል።
በተለይም በቅርቡ የተካሄደውን 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍና በአካባቢው ሁከት ለመፍጠር የውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ከፍተኛ እርብርብ አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ኮማንደሩ የጥፋት ኃይላቱን የሴራ ተልዕኮ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት በመስራት ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ ችለናል ነው ያሉት።
በደብረብርሃንና አካባቢው ህዝብ የሚበጀውንና ሰላሙን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በጽናት መቆሙን የጠቀሱት ኮማንደር ሙሃባው የዚህ ህዝባዊ ትብብር ትልቁ ማረጋገጫና ማሳያ ደግሞ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ስጋት በስኬት መጠናቀቁ ነው ሲሉ አክለው አብራርተዋል።
ከዚሁ የጸጥታና ሰላም ማስከበር ስራ ጋር በተያያዘ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል እሸቴ ከአማራ ፖሊስ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በደብረብርሃን ከተማና አካባቢዋ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የአማራ ክልል 29ኛ እና 30ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል እና የከተማው ፖሊስ ከሌሎች የፌዴራል እና ከክልሉ የጸጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በቅርብ ቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
የከተማው ጸጥታ መዋቅር ከ29ነኛ እና ከ30ኛ ሻለቃ ጋር በመሆን የህዝብን ደህንነት በበቂ ሁኔታ እያስጠበቁ መሆናቸውን ነው ኃላፊው የጠቀሱት።
ይህ በከተማ ደረጃ የሚደረገው የተቀናጀ የህግ ማስከበር ስራ በደብረብርሃንና በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ግዳጅ ላይ ከሚገኙት የ29ኛ እና 30ኛ ሻለቃዎች የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ በአካባቢው ላይ የሚታሰቡ የጥፋት ሴራዎችን በሙሉ ቀድሞ ለማክሸፍ ትልቅ አቅም መፍጠሩን የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊው አመልክተዋል።
የ29ነኛ እና ነ30ኛ ሻለቃ አድማ መከላከልና የከተማው ፖሊስ እንዲሁም ሰላም አስከባሪዎች እና የሚሊሻ አካላት በቅንጅት የሚያደርጉት የሌሊትና የቀን ጥበቃ እንዲሁም የህግ ማስከበር ስራ የደብረብርሃን ከተማን ሰላም አስተማማኝ አድርጎታል ያሉት አቶ ዳንኤል እሸቴ ይህ የጸጥታ አካላት መናበብና ተቀናጅቶ መስራት ህዝባችን ያለምንም ስጋት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲያከናውን አስችሎታል ሲሉ አብራርተዋል።
የ29ኛ ሻለቃ ዘመቻ ክፍል ሀላፊ ዋና ሳጅን ሳሙኤል ደረበ በበኩላቸው በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በተከናወኑ የህግ ማስከበርና የሰላም ጥበቃ ስራዎች አሁን ላይ ማህበረሰቡ የፖሊስን የስራ እሴት በመረዳት የጸጥታው መዋቅር አይንና ጆሮ በመሆን በግንባር ቀደምትነት እየደገፈ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።
የሻምበል አዛዥ ዋና ሳጅን መኳንንት ስመኘው ሲያብራሩ የዋና ጠቅላይ መምሪያው ስትራቴጂክ አመራሮች የሰራዊቱን ዝግጁነትና ፍላጎት ለመፈተሽ እንዲሁም ድጋፍ ለመስጠት ታች ድረስ ወርደው የሚያደርጉት ቀጥተኛ ክትትል ለበለጠ ግዳጅና ለላቀ ቁርጠኝነት አነሳስቶናል። ይህ የአመራሩ ቅርበት ሰራዊቱ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች በወቅቱ እየፈታ በከፍተኛ ሞራል የጀግንነት ስራዎችን እንዲያከናውን አግዟል ብለዋል።
የሰራዊቱ አባላት ያላቸውን የጸና ፖሊሳዊ ስነ-ምግባርና የህዝብ ወገንተኝነት የገለጸችው ደግሞ የ29ኛ ሻለቃ አባል ም/ሳጅን እንዬ ንጉሴ ናት።
እንደ ም/ሳጅን እንዬ ገለጻ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ደህንነት ስንል በርካታ መስዋዕትነቶችን እየከፈልን ሰላምን እያጸናን እንገኛለን፤ ህዝባችን በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን ስትል የሰራዊቱን ጽኑ አቋም አረጋግጣለች።
በሰሜን ሸዋ ዞንና አካባቢው የሚገኘው የ29ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ ሰራዊት አባላት ሌሊት ከቀን በመስራት፣ የህዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላትን በህግ ጥላ ስር በማዋልና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ እያከናወኑት ያለው ተግባር በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ምስጋና እየተቸረው ይገኛል።








