“የጸጥታ ኃይላችን ያስመዘገበው ስኬት የሕዝባዊ ወገንተኝነቱና የሙያዊ ዲሲፕሊኑ ማረጋገጫ ነው” ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“የጸጥታ ኃይላችን ያስመዘገበው ስኬት የሕዝባዊ ወገንተኝነቱና የሙያዊ ዲሲፕሊኑ ማረጋገጫ ነው” ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

በአማራ ክልል 7ኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን በቁርጠኝነት ኃላፊነቱን እየተወጣ ለሚገኘው የጸጥታ ኃይል፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ፣ ለፌደራል ፀጥታና የደህንነት አካላት እየፈፀሙት ላለው የተቀናጀና የተናበበ ተግባር ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ላቅ ያለ ምስጋናና እውቅና አበረከቱ።

መላው ሕዝባችን በነቂስ ወጥቶ የምርጫ ካርድ ያወጣበት ሂደት እና የሚፈልገዉን ለመምረጥ እየተንቀሳቀሰ ያለበት መንገድ እጅግ ከፍ ያለ ክብር የሚሰጠዉ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጀነራሉ ፣ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመምረጥ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ እየተከናወነ መሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ሕዝባችን ሁልጊዜም ሰላም ፈላጊ መሆኑንና ሰላምን ለማስጠበቅ በሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የሰላም አምባሳደርነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝም አፅንኦት በመስጠት ገልፀዋል ።

ይህንን ታላቅ ሀገራዊና ክልላዊ ተልዕኮ ለማደናቀፍ ጸረ-ሰላም ኃይሎች የተለያዩ ሴራዎችን ቢሸርቡም፣ በጀግናዉ መከላከያ ሠራዊትና የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ያደረጉት መፍጨርጨር ሁሉ መና የቀረበትና ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

የምርጫ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ሌሎች በክልሉ የተከናወኑ የምርጫ ቅስቀሳ ፣ የአስመራጭ እና የታዛቢዎች ስልጠና ፣ የምርጫ ቁሳቁሳቁስ ማጓጓዝ ፣ የተፎካካሪ እና የገዥው ፓርቲ የአጩ ትዉዉቅ ፣ የአዳራሽና የጎዳና ላይ ሰልፎች በሁሉም የክልሉ ከባቢዋች በተሳካና ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠዉ ጌዜ ዉስጥ በከፍተኛ ድል እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ኃይላችን የላቀ ጀግንነትና ቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል ያሉት አዛዡ፤ ይህ አኩሪ ተግባር ለጸጥታ ኃይላችን ከፍተኛ ኩራት ለሕዝባችን ደግሞ ትልቅ ክብርን ያተረፈ አድርጎታል ።

“የጸጥታ ኃይላችን ፍጹም ሙያዊ ዲሲፕሊን በተሞላበት እና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ባሳየ መልኩ ሂደቱ የተመራበት፣ የህዝባቸ‍ን ፣ የፀጥታ አካለት ትብብርና ቅንጅት ዉጤት መሆኑን የጠቆሙት አዛዡ፤ የኅብረተሰቡን አደረጃጀት በማጠናከርና ተቀናጅቶ በመሥራቱ ማኅበረሰቡ በሙሉ እምነት ወደ መደበኛ ተግባሩ እንዲመለስ የተደረገው ጥረት እጅግ የሚደነቅና የጸጥታ ኃይሉ አመራርና አባላት የቅንጅት ውጤት መሆኑን ገልፀዋል ።

በአሁኑ ወቅት የክልሉን ሰላምና ደህንነት ሊያደፈርሱና ምርጫውን ሊያስተጓጉሉ ለሚሞክሩ ማናቸውም የጥፋት ኃይሎች የጸጥታ መዋቅሩ የማያወላውል አስተማማኝ ፀጥታን የማስፈን ሙሉ ብቃት፣ ፅናትና ፍፁም አቅም እንዳለው አስገንዝበዋል።

ሕዝቡ በጸጥታ ኃይሉ ላይ ያለው እምነት ይበልጥ እንዲጎለብትና ፍፁም ደህንነት ተሰምቶት የምርጫ ሂደቱን እንዲያጠናቅቅ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን ያረጋገጡት ዋና አዛዡ፤ ምርጫው ያለምንም ኮሽታና የሰላም መጓደል በታላቅ ድል እንዲጠናቀቅ መላው የጸጥታ መዋቅር ከምንጊዜውም በላይ በተጠንቀቅና በማይናወጥ ቁርጠኝነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሉ ሕዝብም የጸጥታ ኃይሉ የራሱ ጋሻና አለኝታ መሆኑን በመረዳት በጸጥታ ኃይሉ ላይ ሙሉ እምነትና መተማመን በመጣል፣ በምርጫው ዕለትም ካርድ ለማዉጣት ያሳየዉን አኩሪ ተግባር እንዲፈፅም ፣በነፃነት ወጥተው የሚፈልጉትንና ያመኑበትን መምረጥ የሚችሉ መሆኑን ኮምሽነር ጀነራሉ በድጋሚ አፅንኦት በመስጠት ገልጸዋል።

በመጨረሻም ሕዝባችን በምርጫው ሂደትም ሆነ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የትኛውንም ዓይነት የጸጥታ ችግር ወይም አጠራጣሪ ሁኔታ ሲመለከት፣ በተለመደው የስልክ መስመር ጥቆማ ከማድረግ ባለፈ፣ አዲሱን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP app) በመጠቀም በጽሑፍ፣ በምስልና በድምጽ ፈጣን ጥቆማ በመስጠት ሰላሙን በጋራ እንዲያስጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top