“የትራፊክ አደጋዎችን በመቀነስ የሕዝብን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከጉዳት መጠበቅ የቀዳሚነት ትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባል!” ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ
በመንገድ ትራፊክ እና ትራንስፖርት ቁጥጥር ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እና የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕግ ምክር ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት የክልል ዐቃቢ ሕግ አቶ ይስማው ዘመነ ለፈፃሚ አካላት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል።
የስልጠናው ዋና ትኩረት በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መንገድ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቢሮ መካከል ሊከናወኑ የሚገባቸውን የሥራ ድርሻዎች በግልጽ መለየት ላይ ያተኮረ ነበር።
በዚሁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ፣ የአብክመ የመንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ስራው፣ የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች፣ የቢሮው ምክትል ኃላፊዎች እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች እንደገለጹት የተቋማትን የሥራ ድርሻ በግልጽ ባለማወቅ የሚፈጠሩ የአሠራር ችግሮችን ማስወገድ፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር፣ ሕገወጥ ተግባራትን መከላከልና ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ በበኩላቸው የትራፊክ እና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ህጎችን አጥብቆ ማስከበር፣ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እና የቁጥጥር ሥራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
“የትራፊክ አደጋዎችን በመቀነስ የሕዝብን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከጉዳት መጠበቅ ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባል!” ሲሉ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
የአብክመ የመንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የታቀዱ ዕቅዶች ባልተበረዘ ሁኔታ መሬት ላይ መውረዳቸውን ማረጋገጥ፣ አሠራር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በጊዜ በመለየት የእርምት እርምጃ መውሰድ እና ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኃላፊው አክለውም የተከናወኑ ተግባራት ዋጋ የሚኖራቸው በውጤት ሲለኩ እና ኃላፊነቶች በግልጽ ተሰጥተው በቁጥጥር ሲደገፉ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በመድረኩ የትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ህገ-ወጥ አሰራሮችን ከመሰረቱ ለማስቀረት የተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎና ጥብቅ የህግ ማዕቀፍ ወሳኝ መሆናቸው ተስመርቦበታል።
















