የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ2019 ዓ/ም የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የ2019 ዓ/ም የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ።

የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥን ጨምሮ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች፣ የዋና መምሪያ እና የመምሪያ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች የ2019 ዓ.ም የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርትን አቅርበዋል።

ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንደገለጹት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል።

ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ከአጎራባች ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር የነበረው በቅንጅታዊ አሰራር በቀረበው ሪፖርት በመልካም ጎን ተመላክቷል።

ከሀገር ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ከክልሉ አጋር የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ በህገወጥ ቡድኖች ላይ እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ተግባር እና በክልሉ የተከወኑ ሁነቶች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ማድረግ መቻሉ በጥንካሬ ተጠቅሷል።

የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ኃይሉ ስነ-ምግባርን ተላብሶ የመዋጋት አቅሙን እና የግዳጅ አፈጻጸሙን ለማሳደግ በአራት ቀጠናዎች ከአጋር አካላት ጋር እና በተናጠል በተሰማራባቸዉ ግዳጆች ጠንካራ ውጤት እያስመዘገበ እንደነበር በሪፖርቱ ተገልጿል።

በተጨማሪም ለልዩ ልዩ ሙያተኞች የስራ ላይ ስልጠና መሰጠቱ በሩብ ዓመቱ ከተከናወኑ አንኳር ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ስኬቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ጤናማ የመንገድ ትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የትራፊክ ፖሊሶች ከአጋር አካላት ጋር ባከናወኑት ተግባር የተሻለ አፈጻጸም መመዝገብ መቻሉም ተመላክቷል።

የመረጃ አያያዝ ስርአቶችን ማስተካከል በወንጀል ምርመራ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ የወንጀል ጥቆማዎችን እና አቤቱታዎችን በስታንዳርዱ በማጣራት በኩል የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸው ተገልጿል።

የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እና የአሰራር ቅልጥፍናን ለመፍጠር ያለመ የዲጂታላይዜሽን ስልጠና በዞን ደረጃ መሰጠት መጀመሩ ተጠቁሟል።

ከተወያዮቹ ለተነሱ ሀሳብች እና አስተያየቶች ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥን ጨምሮ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥን በሰጡት ማጠቃለያ የአማራ ክልል ፖሊስ እየከወነ ያለውን በሁለንተናዊ ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የህዝብን እምነት እንደገና በመገንባት፣ ዜጎችን በመጠበቅ፣ ፍትህን በማስፈን እና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ ማተኮር እንዳለበትም ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ገልጸዋል።

ከፌደራል እና ከክልሉ የጸጥታ እና ፍትህ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናክር የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ ስራን በማሳደግ በክልሉ ፍትህ እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ድርሻ ልናበረከት ይገባል ሲሉ አክለዋል።

የሚሰጠውን ተልዕኮ እና ግዳጅ በአመርቂ ውጤት መፈጸም የሚችል የፖሊስ ኃይል መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉ ነው ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።

ህገ-ወጥ ቡድኖች የቀሩትን የጥፋት ቀዳዳዎች ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮች የጥንቃቄ እና የዝግጁነት ሥራዎችን አጠናክረው ይቀጥላሉ።

የኦፕሬሽናል ዕቅዶችን ከማስፈጸም ባለፈ፣ በቀጣይ የወንጀል መከላከል ስራዎች እና የሕግ ማዕቀፎችን በማጠናከር አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሥራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የክልላችንን ሰላም እና ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከህዝቡ ጋር በመተባበር የሚከናወኑ የጸጥታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ነጥቦች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ተጠናቋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top