“የመንግስትና የህዝብ አደራችሁን በመወጣት ወርቃማ የታሪክ አሻራ አስቀምጣችኋል!” ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ

“የመንግስትና የህዝብ አደራችሁን በመወጣት ወርቃማ የታሪክ አሻራ አስቀምጣችኋል!” ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በማስመልከት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፈለገ-ህይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ተገኝተው የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን በመጎብኘት የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር አካሂደዋል።

በቦታው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራልና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ “እናንተ ለሕዝብ ሰላምና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር የማያልፍ ወርቃማ ገድል በመፈፀም ደማቅ ታሪክ የጻፋችሁ ጀግኖች ናችሁ” ብለዋል።

የክልላችንን ሰላም ለማደፍረስ ብሎም ሀገራችንን ለማፍረስ ከምንጊዜም የውጭ ጠላቶቻችን እና የሀገር ውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ ውድ ዋጋ የከፈላችሁ የቁርጥ ቀን ልጆች ናችሁ ሲሉ ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም ሀገርን ከመፍረስና ሕዝብን ከእንግልት ለመታደግ በገባችሁትት ቃል ኪዳን መሰረት ለከፈላችሁት መስዋዕትነት የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ኩራት ይሰማዋል ነው ያሉት።

ለእናንተ የሚሰጠው ክብር በቃላት ብቻ የሚነገር አይደለም ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር እየተገነባ ያለው የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ሲጠናቀቅ ሰራዊቱ የተሻለ አገልግሎት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።

ማዕከሉም ከማገገሚያነት ባለፈ ራስን ለመቻል የሚያግዙ የሙያ ስልጠናዎች የሚሰጡበትና ለአባላቱ ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የሚገነባ መሆኑንም የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዡ አብራርተዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው፣ የፀጥታ አባላቱ የሕዝብን አደራ በብቃት የተወጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በችግሮች ሳትበገሩ ያለፋችሁ፣ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትናችሁ ለግዳጅ የበቃችሁ እና ውድ ዋጋ የከፈላችሁ በመሆናችሁ ተቋሙ ዘላለማዊ ታሪካችሁን ይዘክራል ሲሉም አመስግነዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ተቋሙ ለሰራዊቱ ያለውን ከፍተኛ ክብር የሚያሳይና በአመራሩ እና አባሉ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው ገልጸዋል።

በመጨረሻም አመራሮቹ ለሀገር ሰላምና ደህንነት ሲባል በተለያዩ ግንባሮች መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ አካላት እና ለመላው ማህበረሰብ በሙሉ እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት አደረሳችሁ ብለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top