በምዕራብ ጎንደር ዞን ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመግታት በተደረገ ጥብቅ ክትትል፣ 80 በርሚል ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።
በሀገሪቱ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የሚጥሩ ህገ-ወጦች ላይ የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ በቁጥጥር ስር እያዋለ ይገኛል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን አብራሐ ጅራ ቀበሌ 01 ልዩ ስሙ ኬላ አካባቢ ፖሊስ ባደረገው ጥብቅ ፍተሻ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 80 በርሚል ነዳጅ መያዝ መቻሉን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ምስጋነው ካሴ ገልጸዋል።
እንደ ኮማንደር ምስጋነው ካሴ ገለጻ በፖሊስ ክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ 80 በርሚል ናፍጣ በህገ-ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ፤ 2 አይሱዚ መኪናዎች ነዳጁን ሲያጓጉዙ የነበሩ ከሁለቱም አሽከርካሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ፖሊስ ከሌሎች አጋር የጸጥታ አካላት እና ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው መረጃን መሠረት ያደረገ ክትትልና ቁጥጥር የክልሉን ኢኮኖሚ የሚጎዱ ተግባራትን ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።
የህዝብን ደህንነትና የሀገር ሀብት መጠበቅ ቀዳሚ ተግባሩ የሆነው ፖሊስ ህገ-ወጦችን በመከላከል ውጤታማ ስራ እየከወነ መሆኑን ጠቁመው ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት ለተባበሩ ነዋሪዎች ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የጸጥታ ኃይሉ የነዳጅ እጥረትን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ዝውውሮች፣ ኮንትሮባንድና የሸቀጦች መደበቅ ላይ የጀመረውን ቁጥጥርና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የተከናወነው ስኬታማ ኦፕሬሽን ለህገ-ወጦች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል ያሉት አዛዡ በየኬላዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻና ድንገተኛ አሰሳዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የጋራ ሀብታችንን ከደላሎችና ከህገ-ወጦች ሴራ በመከላከል ረገድ ሁሉም የሚጠበቅበትን የዜግነት ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ኮማንደር ምስጋነው ካሴ አሳስበዋል።


