ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች የምረቃና የማዕረግ ሽግግር ስነ-ስርዓት በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ

ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች የምረቃና የማዕረግ ሽግግር ስነ-ስርዓት በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ

በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩና ወደ ከፍተኛ የማዕረግ ሽግግር ያደረጉ የፖሊስ መኮንኖች በደመቀ ሁኔታ ተመርቀዋል።

ተመራቂ መኮንኖቹ በስራ አፈጻጸማቸው ውጤታማ እና ለከፍተኛ አመራር ብቁ መሆናቸው የተመሰከረላቸው ናቸው።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ባስተላለፉት መልዕክት ስልጠናው መኮንኖቹ ወደ ላቀ የአመራር እርከን ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን ስልታዊ እና ተግባራዊ እውቀት እንዲጨብጡ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ገለጻ ዛሬ የሚመረቁ እነዚህ ከፍተኛ መኮንኖች በቆይታቸው በተግባር ተፈትነው የተሻለ የአመራር ብቃት ያሳዩ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸውን በአግባቡ የሸፈኑ እና አርዓያ የሚሆን ፖሊሳዊ ስብዕና የተላበሱ ናቸው ብለዋል።

ይህ ማዕረግ በስራቸው ላሳዩት ትጋት እውቅና የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ለሚጠብቃቸው ትልቅ የህዝብና የመንግስት አደራ ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ከመቸውም ጊዜ በላይ በጠንካራ መንፈስ እና በግንባር ቀደምትነት ችግሮችን በመጋፈጥ ከራስ በፊት የህዝብን እና የሀገርን ጥቅም የሚያስቀድም የፖሊስ አመራር እና አባላት ማፍራት ቅድሚያ የሚሰጠው የተቋማችን የዕለት ከዕለት ተግባር ነው ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት አጽንኦት ተሰጥተው አብራርተዋል።

ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ አክለውም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የፖሊስ ሰራዊቱን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግና ተቋማዊ ለውጡን ለማፋጠን የጀመረውን የሰው ኃይል የማብቃት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዕለቱ የማዕረግ እድገት የተቀበሉ ተመራቂ መኮንኖች በሰጡት አስተያየት የተሰጣቸው አዲስ ማዕረግ ስልጠና በኃላፊነት ስሜት የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የበለጠ እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል።

እንደ ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች ገለጻ ይህ ስልጠና በዘመናዊ የፖሊስ አመራር ጥበብ ዙሪያ የነበረንን እውቀት ያሰፋልን ነው ብለዋል።

የተሰጠንን የከፍተኛ መኮንንነት ማዕረግ በክብር በመያዝ፣ ህዝባዊ ወገንተኝነታችንን በተግባር ለማሳየትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ ተመራቂዎቹ ቃል ገብተዋል።

የእለቱ ተመራቂዎች በቆይታቸው በንድፈ-ሃሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን በቀጣይ በየተመደቡበት የስራ ዘርፍ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተመራቂ የፖሊስ መኮንኖች ለአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ 114 አጋዥ መጻሕፍት በስጦታ አበርክተዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች፣ ከፍተኛ የመከላከያ አመራሮች፣ የክልል እና የዞን የስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ታድመዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top