የጸጥታ ኃይሉ በአሳግርት ወረዳ በወሰደው የተቀናጀ እርምጃ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኑ አመራሮችና አባላት ተደመሰሱ
በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው የጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው በነበሩ የህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድን አመራሮችና አባላት ላይ የ112ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት በወሰዱት ድንገተኛ ኦፕሬሽን እርምጃ መወሰዱን አስታወቁ።
በወረዳው አንጎለላ ጠራ አንጋዳ ቀበሌ ላይ በተካሄደው ኦፕሬሽን ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቡድኑ አባላት የተደመሰሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የነጎድጓድ ክፍለ ጦር መሪ የነበረው ይገረም ከበደ እና ሱራፌል የተባለ ሌላኛው አመራር ይገኙበታል።
በጥቃቱ በአጠቃላይ 2 የቡድኑ አመራሮችን ጨምሮ 18 የቡድኑ አባላት የተደመሰሱ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ ሴሎችና አባላትም ከነሙሉ ትጥቃቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በኦፕሬሽኑ ወቅትም 4 የጠላት ሴሎች፣ 4 የክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች (ጥቁርና ታጣፊ) እንዲሁም 2 የካሜራ ድሮኖች ከነመቆጣጠሪያቸው ተማርከዋል።
ጥምር ጦሩ ከጉርሜዳ ዋዩ እስከ ታች ሙጠር ባሉ የጠላት መሸሸጊያዎች ላይ ጠንካራ ስምሪት እያከናወነ ይገኛል።
የ3ኛ ሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ሬና መንገሻ እንደገለጹት፣ ቡድኑ ቀደም ሲል በንፁሃን ዜጎች ላይ ዘግናኝ ግድያና ዝርፊያ ሲፈፅም የቆየ መሆኑን ጠቅሰው አሁን የተገኘው ውጤት የጸጥታ ኃይሉን ብቃትና የተቀናጀ ኦፕሬሽን የመምራት ጥንካሬ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ቀጠናውን ከማንኛውም የፀረ-ሰላም ኃይሎች የማፅዳት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ይህ ስኬታማ እርምጃ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይልና ሌሎች አጋር አካላት ያላቸውን የማይበገር አንድነትና ለህዝብ ሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።
ህብረተሰቡም ከግጭት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ በመረዳት ለጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ለዘላቂ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።


