ጥምር ጦሩ የእብናት ከተማን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር አዋለ
በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘው የጥምር ጦር ባከናወነው የተቀናጀ ኦፕሬሽን፣ ለተከታታይ ቀናት በጽንፈኛው ቡድን ቁጥጥር ስር የነበረችው የእብናት ከተማ ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋሏ ተገለጸ።
በአካባቢው ህግ የማስከበር ግዳጅ ላይ የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሌላ ሀገራዊ ተልዕኮ ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ፣ ከተማዋ ላለፈው አንድ ወር ገደማ በህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኑ ተይዛ መቆየቷ ይታወሳል።
ሆኖም የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በዛሬው ዕለት በወሰዱት ፈጣንና አስደናቂ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ከተማዋንና አካባቢዋን ከአጥፊው ቡድን ነፃ ማድረግ ችለዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ በፈጸመው በዚህ ግዳጅ ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እየተመለሰች ሲሆን፣ የጥምር ጦሩ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለውን ፀጥታ ሙሉ በሙሉ እያረጋገጠ እንደሚገኝ ታውቋል።
የተገኘው ድል በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ ሲሆን፣ ሰራዊቱ የከተማዋንና የወረዳውን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።



