በደቡብ ጎንደር ዞንና በደብረ ታቦር ከተማ የጸጥታ መዋቅሩን የመፈጸም አቅም በማሳደግ የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
የጸጥታ መዋቅሩን የማድረግና የመፈጸም አቅም በማሳደግ የህግ ማስከበር ስራን አጠናክሮ በመስራት የዞኑንና የከተማውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከደቡብ ጎንደር ዞን ከደብረ ታቦር ከተማ እና በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ አካላት ጋር በወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የዞኑ እና የከተማው የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች የዞኑንና የከተማዋን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት በመስራት የህግ ማስከበር ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትና ህብረተሰቡም በመደራጀት የአካባቢው የጸጥታ ባለቤት መሆን እንደሚገባው ተገልጿል።
በመድረኩ የተገኙት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት የጸጥታ ችግሮቹ የሀገርን ሰላም ለመንሳት በሩቅና በቅርብ ጠላቶች የሚታቀዱ ሴራዎች መሆኑን ገልጸዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከህዝቡ ጋር በትብብርና በቁጭት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
ኃላፊዎቹ አያይዘውም የህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድን የውጭ ጠላቶችን ተልዕኮ በመቀበል በህዝብ ላይ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን አንስተው በየደረጃው ጠንካራ የጸጥታ አደረጃጀት በመፍጠር ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በርካታ ህገ-ወጥ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን የጠቀሱት የስራ ኃላፊዎቹ ይህን የሰላም ሂደት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በቅንጅት መከላከልና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የጸጥታ መዋቅሩ አባላትና አመራሮች የማድረግና የመፈጸም አቅማቸውን በማሳደግ፣ ለዞኑና ለከተማው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።




