በአማራ ክልል ያለአግባብ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መጀመሩ ተገለጸ

በአማራ ክልል ያለአግባብ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መጀመሩ ተገለጸ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ፣ የነዳጅ ዋጋ መስተካከልን ምክንያት በማድረግ ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ።

የሀገር ውስጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚያችን እድገት ወሳኝ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ አሰራሮች በህብረተሰቡ ላይ ጫና እየፈጠሩ እንደሚገኙ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል።

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ባደረገው የክትትል ስራ፣ ህዝብን ለከፍተኛ እንግልትና ምዝበራ የሚዳርጉ አካሄዶችን ለመግታት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

በህግ ከተወሰነው ታሪፍ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም የዋጋ ጭማሪ በዝቅተኛው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ ይህን ህገ-ወጥ ተግባር ለመከላከል ፖሊስ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ሲል የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አረጋግጧል።

ለትርፍ ሲባል ተሽከርካሪን ከአቅም በላይ መጫን ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስኤ ነው ያለው ጠቅላይ መምሪያው ይህ ድርጊት የዜጎችን ህይወት ለአደጋ የሚያጋልጥና ንብረትን የሚያወድም በመሆኑ በምንም መልኩ ሊታለፍ አይገባም ብሏል።

የትራንስፖርት ማህበራት አባሎቻቸው ህግና መመሪያን አክብረው እንዲሰሩ የክትትልና ቁጥጥር ስራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርቧል።

ማንኛውም የትራፊክ ፖሊስ አባል ሙያዊ ስነ-ምግባሩን በጠበቀ መልኩ ግዴታውን እንዲወጣና ህግ በሚጥሱ አካላት ላይ ያለምንም ድርድር እርምጃ እንዲወስድ ዋና ጠቅላይ መምሪያው መመሪያ አስተላልፏል።

የቁጥጥር ስራው ውጤታማ እንዲሆን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥምና ትርፍ ጭነው ሲመለከት አቅራቢያ ለሚገኝ የትራፊክ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠትና መረጃ በማጋራት የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል።

የትራፊክ እንቅስቃሴው የተሳለጠ እንዲሆንና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የምናደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።

የተቀናጀ ስራው የህዝቡን የትራንስፖርት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ በመኆኑ በህገ-ወጥ ተግባር ላይ በሚሰማሩ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ እንደሚሆን ዋና ጠቅላይ መምሪያው አረጋግጧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top