ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባህር ዳር የልማት ስራዎችን ጎበኙ
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር በመገኘት የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በከተማዋ የተጀመሩ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን አረጋግጠዋል። እነዚህ ስራዎች የባህር ዳርን ገጽታና ውበት በከፍተኛ ሁኔታ የለወጡና ያስዋቡ መሆናቸውም በምልከታው ወቅት ተገልጿል።
እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች ጉብኝት በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑንና የጸጥታ ኃይሉ የጥፋት ቡድኖችን በመመከት እያስመዘገበ ያለውን ድል ያረጋገጠ ሆኗል።
ከፍተኛ አመራሮቹ በከተማዋ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመመልከት፣ የሀገርን ገጽታ የሚቀይሩና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ይህም ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በከተማዋ መገኘታቸው በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሀገርን ለማፍረስና ህዝብን ለማወክ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተመሳጥረው የሚሰሩ ህገ-ወጥ ቡድኖችን በመመከት ረገድ ደማቅ ታሪክ እያስመዘገበ መሆኑ ተመላክቷል።
የጸጥታ አካላቱ የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ውድ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑም ተጠቁሟል።
ህዝቡ እነዚህ ህገ-ወጥ ቡድኖች ከባዕድ ኃይሎች ጋር በመሆን ሀገርን የመበተን ሴራ እያከናወኑ መሆኑን ተገንዝቦ፣ የተጀመረው የልማትና የሰላም ጉዞ ዳር እንዲደርስ ከመንግስትና ከጸጥታ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።
በአሁኑ ወቅት በባህር ዳርና አካባቢው ያለው ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይ በመሆኑ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና የጥፋት ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተረጋግጧል።





