የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የ13ኛው ዙር የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ሰልጣኞችን አስመረቀ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በታክቲክ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሲያሰለጥናቸው የቆያቸውን የ13ኛ ዙር ሰልጣኝ ፖሊሶች በዛሬው ዕለት በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ፣ የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክና ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት የክልሉን የጸጥታ መዋቅር በዕውቀትና በክህሎት ለማዘመን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይም የወንጀል ምርመራ ሂደትን በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራትና የፍትህ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ተቋሙ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ይህ የ13ኛው ዙር ምርቃም የክልሉን ፖሊስ የምርመራ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የታለመው ስትራቴጂ አካል መሆኑ ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተመራቂ ሰልጣኞች በቆይታቸው የቀሰሙትን ቲዎሪያዊና ተግባራዊ ዕውቀት ወደ መሬት በማውረድ የህዝባቸውን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቁ አሳስበዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ገለጻ ወንጀልን የመከላከልና የመመርመር ስራ ከፍተኛ ስነ-ምግባርንና ሙያዊ ብቃትን ይጠይቃል።
እናንተ ዛሬ ስትመረቁ የህዝብን አደራ ተሸክማችሁ ነው፤ በመሆኑም በምርመራ ሂደት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር የላቀ ውጤት እንደምታስመዘግቡ እምነቴ ጽኑ ነው ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎትን ለመገንባት የሚያደርገውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባዬ በበኩላቸው፣ ምርመራ ስራ በቴክኖሎጂና በዘመናዊ ስልቶች መታገዝ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኮማንደር ዳምጤ ባዬ አክለውም ወንጀል በአሁኑ ወቅት መልኩንና ስልቱን እየቀየረ በመምጣቱ ምርመራውም በተመሳሳይ መልኩ በዕውቀትና በጥበብ መመራት ይኖርበታል ብለዋል።
በተለይም የሙስና ወንጀሎችን ጨምሮ ውስብስብ ወንጀሎችን በብቃት ለመመርመርና ለፍትህ ለማቅረብ እናንተ ዛሬ የያዛችሁት የታክቲክ ምርመራ ዕውቀት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ሲሉ ገልጸዋል።
ተመራቂ ሰልጣኞች በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የነበራቸው ቆይታ የወንጀል ምርመራ ጥበብንና ስልቶችን በጥልቀት እንዲረዱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
በተለይም የተወሳሰቡ ወንጀሎችን በቀላሉ የመተንተንና በማስረጃ የማስደገፍ አቅማቸው ማደጉን ጠቁመዋል።
የተጣለብንን ሀገራዊ እና ክልላዊ ኃላፊነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
በዕለቱ በስልጠናቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሰልጣኞች የሽልማትና የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ተከናውኗል።









