የተቀናጀ የጸጥታ ስራ ውጤት!
በአማራ ክልል የ1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም ተጠናቀቀ፤ የክልሉ ፖሊስ ለህዝቡና ለጸጥታ ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል።
በመላው የአማራ ክልል የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የ1447ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልን በድምቀትና በሰላም አክብረው ማጠናቀቃቸው ተገለጸ።
በዓሉ በክልሉ ሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች በሚገኙ መስጂዶች እንዲሁም በታላላቅ አደባባዮች የእምነቱ ተከታዮች በነጻነትና በደስታ አክብረውታል።
ለበዓሉ ሰላማዊ መሆን የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና የጸጥታ ኃይሉ ቅንጅታዊ ስራ ውጤታማ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል።
የእምነቱ ተከታዮችና መላው የክልሉ ህዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት በመስራትና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን በመጠቆም የበዓሉን ሰላም አስጠብቀዋል።
የክልሉ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች በጋራ ባደረጉት ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ በዓሉ ምንም ዓይነት የጸጥታ ስጋት ሳይገጥመው እንዲጠናቀቅ አስችለዋል።
በዓሉ የሀይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶችን ባንጸባረቀ ሁኔታ በድምቀት ተከብሯል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት ላሳዩት የሀይማኖት አባቶች፣ ለወጣቶችና ለመላው የጸጥታ ኃይል የላቀ ምስጋና አቅርቧል።
ይህ በቅንጅት የተሰራው የሰላም ስራ በቀጣይም ለማንኛውም ማህበራዊ እና ህዝባዊ ሁነቶች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል።
የጸጥታ ኃይሉ የህዝቡን ደህንነትና የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።

