“ረመዳን የሰላምና የመረዳዳት እሴቶቻችንን የምናጸናበት ነው!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“ረመዳን የሰላምና የመረዳዳት እሴቶቻችንን የምናጸናበት ነው!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለ1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጀመሪያ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ ለክልላችን ህዝቦች፣ ለክልሉ ፖሊስ ሰራዊትና የጸጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስ እና ለደኅንነት አካላት በሙሉ፤ እንኳን ለ1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

የረመዳን ወር የሰላም፣ የፍቅር፣ የመረዳዳት እና ራስን በመግራት ለፈጣሪ የሚገዙበት ታላቅ መንፈሳዊ ወር ነው።

የእምነቱ ተከታዮች በዚህ ቅዱስ ወር በጾምና በጸሎት ያሳለፋችሁት ጊዜ ለግል ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገራችን ሰላም፣ ለህዝቦች አንድነትና ለጋራ እድገት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለን እናምናለን። ይህ መንፈሳዊ ጽናትና መተሳሰብ ከበዓሉ በኋላም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል።

በዓሉ ሲከበር የተቸገሩትን በመርዳትና እጃችሁን በመዘርጋት፤ የታመሙትን በመጠየቅና አብሮነትን በማሳየት እንዲሁም በመካከላችን ያለውን የቆየ ወንድማማችነት እና አብሮ የመኖር እሴት በማጠናከር ሊሆን ይገባል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ህዝባችን ያለምንም የጸጥታ ስጋት በዓሉን በድምቀትና በሰላም እንዲያከብር አስፈላጊውን ዝግጅት በሙሉ አቅሙ አድርጓል።

የጸጥታ ኃይላችን ህዝባዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።

‘ሰላም የሁላችንም የጋራ እሴት ነው!’ በመሆኑም ህዝባችን እንደተለመደው ከፖሊስ ሰራዊቱ ጋር በቅርበት በመቀናጀት እና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መረጃ በመስጠት ለሰላም መረጋገጥ የበኩሉን ታሪካዊ ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቀርባለሁ።

በድጋሚ በዓሉ የሰላም፣ የጤና እና የደስታ እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ።

ኢድ ሙባረክ!

ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top