የሙስሊሙ ማህበረሰብ የዘንድሮውን በዓል በሙሉ ደስታና በታላቅ ድምቀት እንዲያከብር፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከጸጥታ ግብረ-ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለሰላም ዘብ መቆሙን ገለጸ።
1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በመላው የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ፣ በፍቅር እና በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ አስታውቋል።
በዓሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቅ መንፈሳዊ ክንውን ከመሆኑም ባለፈ፣ ኢትዮጵያዊ የአንድነት፣ የመከባበርና የመረዳዳት እሴቶች የሚንጸባረቁበት በመሆኑ በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ኃይሉ ከፍተኛ ዝግጅትና የሰው ኃይል ስምሪት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ገልጸዋል።
የኢድ ሶላት በሚከናወንባቸው መስጊዶችና አደባባዮች ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከጸጥታ ግብረ-ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ከመቼውም ጊዜ የተለየ የተቀናጀ ስምሪት በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱን ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ጠቁመዋል።
የኢድ በዓል የአንድነታችን ውበት፣ የመተሳሰባችን መገለጫ በመሆኑ ይህ እሴት ተጠብቆ እንዲቀጥል የጸጥታ ኃይሉ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቅሰዋል።
በዓሉን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን የጸጥታ ኃይሉ በልዩ ትኩረት እየተከታተለ ይገኛል። ማንኛውንም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ተግባራት ላይ የጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ሙሉ ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ገለጻ ፤ የጸጥታ ኃይሉ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ኩነቶችን በስኬት የመጠበቅ የላቀ ልምድ ያለው በመኆኑ፣ የዘንድሮውን የኢድ አልፈጥር በዓልም በሰላም ለማጠናቀቅ ሙሉ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል። ህዝበ ሙስሊሙ ያለምንም ስጋት በዓሉን እንዲያከብር የጸጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ጥበቃ ሁሉ ያከናውናል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በተለይም በበዓል ሰሞን የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በበዓሉ ዕለት የሚታየውን የሰዎችና የተሽከርካሪዎች ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠርና አደጋ እንዳይደርስ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በልዩ ትኩረት እንደሚያሰማራም ተናግረዋል።
የኢድ አልፈጥር በዓልን ተከትሎ የሚታየውን ከፍተኛ የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሽፋን በማድረግ፣ ወቅታዊውን የነዳጅ እጥረት እንደ ምክንያት በመጠቀም ባልተገባ መልኩ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ህግና ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይም ተገቢው ቅጣት እንደሚያደርግም የጸጥታ ኃይሉ አጽንኦት ሰጥቶ እየሰራ እንደኆነ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
ሰላም የጋራ እሴት በመሆኑን የጠቀሱት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ህብረተሰቡ ለጸጥታ ኃይሉ እያደረገ ያለውን የተለመደ ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።ማንኛውንም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥሙ በአቅራቢያ ለሚገኝ የጸጥታ አካል ጥቆማ በመስጠት ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን አሳስበዋል።
ለመላው ህዝበ ሙስሊም በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የፍቅር እንዲሆን በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም መልካም ምኞትን ገልጸው፤ የጸጥታ ኃይሉ የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

