በክልሉ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርና ንግድ ለመግታት ጥብቅ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል።

በክልሉ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርና ንግድ ለመግታት ጥብቅ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ እየታየ ያለውን የነዳጅ እጥረት ተገን በማድረግ፣ በሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድና ዝውውር ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ለህዝብ ይፋ ያደርጋል ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ለማባባስና የሕዝቡን ማኅበራዊ ህይወት ለማናጋት፣ ወቅታዊውን የነዳጅ እጥረት ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ሰፊ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያከናወነ ይገኛል።

ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ከፍተኛ ክትትልና በኬላዎች ላይ በተከናወነ ፍተሻ፣ በርካታ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር ሙከራዎች መክሸፋቸውንና በድርጊቱ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ተገቢውን የሕግ ቅጣት እንዲያገኙ መደረጉን መምሪያው ያረጋግጣል።

ይህ ሕገ-ወጥ ድርጊት በጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጸም ቢሆንም፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ግን እጅግ የከፋ ነው።

መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገባቸው የነዳጅ ምርቶች ለታለመላቸው የልማት ሥራዎች ሳይውሉ መባከናቸው አገራዊ ኪሳራን ከማስከተሉ በተጨማሪ የትራንስፖርት ዋጋ እንዲንርና የሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብስ ተግባር በመሆኑ ፖሊስ ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርጋል።

የነዳጅ እጥረት የሕዝብ ትራንስፖርትን በማሽመድመድ ዜጎች ወደ ሥራና ትምህርት እንዳይሄዱ እንቅፋት በመሆኑ ህገወጦችን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል።

ከተፈቀደው የዋጋ ተመን ውጭ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ነዳጅ በመደበቅ ሰው ሠራሽ እጥረት የሚፈጥሩና ከሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ጋር የሚተባበሩ ማደያዎች ላይ የማያዳግም አስተዳደራዊና የወንጀል ክስ እርምጃ ይወሰዳል።

ጨለማን ተገን በማድረግ ነዳጅ ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚያንቀሳቅሱ፣ በማከማቸት ለጥቁር ገበያ የሚያዘጋጁና በማደያዎች ላይ በኃይልም ሆነ በማግባባት ነዳጅ የሚያስቀዱ አካላት ላይ ፖሊስ ያለ ምንም ምሕረት ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል።

የነዳጅ እጥረቱን ተከትሎ የሕዝብን እንግልት ለግል ጥቅማቸው ማዋል የሚፈልጉ አካላትን በምንም ዓይነት ሁኔታ አንታገስም።

የክልላችን ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት የሚጠበቀው በጋራ በምናደርገው ጥረት በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ይህን ሕገ-ወጥ ድርጊት በመጸየፍና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ለቅርብ ፖሊስ ጣቢያ በመጠቆም የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጥሪውን ያቀርባል።

በአሁኑ ወቅት ፖሊስ የኬላ ቁጥጥሩን ከወትሮው በተለየ በማጠናከር፣ የነዳጅ ሥርጭቱ ሕጋዊ መስመር መያዙን ለማረጋገጥ ሌሊትና ቀን እየሠራ እንደሚገኝ እናረጋግጣለን።

በጀግንነት መጠበቅ በሰበአዊነት ማገልገል!!

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 2018 ዓ.ም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top