የወንጀል ምርመራ ሂደትን በቴክኖሎጂ ለማገዝ እና የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነገረ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን ሁለንተናዊ የዲጅታላይዜሽን ሥራ ተከትሎ፣ የወንጀል ምርመራ ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል በማደራጀት ረገድ ውጤታማ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የምርመራ ሥራውን ከወቅቱ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር በማቀናጀት፣ የወንጀል ድርጊቶችን በትክክለኛ ማስረጃ የማረጋገጥና ተጠያቂነትን የማስፈን አቅሙን እያሳደገ ይገኛል ሲሉ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ገልጸዋል።
ተቋሙ የምርመራ ሥራውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እያከናወናቸው ካሉ ቁልፍ ተግባራት መካከል የምርመራ ሥራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ፣ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን የተከተሉ የምርመራ ሂደቶችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አዛዡ ጠቁመዋል።
የምርመራ ሙያ ድፍረትን፣ ፈጠራንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዕውቀትን የሚጠይቅ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያም በቴክኖሎጂ የበለጸገ በአዕምሮው የዳበረ የምርመራ ባለሙያን ለማፍራት በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መረጃን በጥራት ለማደራጀትና በወንጀለኞች ላይ ተጨባጭ ማስረጃ በማቅረብ የፍትህ ሂደቱን ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን የሚጸየፍ አዲስ ተቋማዊ ባህል እየተገነባ መሆኑን የጠቀሱት አዛዡ ፖሊስ ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት ከማሳደጉም በላይ በተቋሙና በሕዝቡ መካከል ያለውን እምነት የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።
ተቋሙ ማንኛውንም ዓይነት አድሎአዊ አሠራር የሚጸየፍና ለሕግ የበላይነት በቁርጠኝነት የሚቆም አሠራር መዘርጋቱን ተከትሎ የምርመራ ሂደቱ ፍትሐዊ፣ ግልጽና ገለልተኛ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ፖሊስ ምንም ቢታጠቅ ምንም ቢዘምን ያለ ህዝብ ድጋፍ ህግ ማስከበር አይችልም ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ህግን ጥሰው ስልጣን ለመያዝም ሆነ በአቋራጭ ለመበልፀግ የሚሯሯጡ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ማህበረሰቡ ተከታትሎ ለጸጥታ ኃይሉ መረጃ በመስጠት ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
በቀጣይም ተቋሙ በቴክኖሎጂ የበለጸገ እና በአዕምሮው የዳበረ የምርመራ ባለሙያ የማፍራት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው አረጋግጠዋል።

