በጎንደር ከተማ ግድያ ፈጽሞ ተሰውሮ የነበረው ተጠርጣሪ እርምጃ ተወሰደበት።
በጎንደር ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ ‘ቅዳሜ ገበያ’ መስጊድ አካባቢ ግድያ ፈጽሞ ተሰውሮ የነበረው ተጠርጣሪ ከጸጥታ አካላት ጋር በፈጠረው ግጭት እርምጃ እንደተወሰደበት የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የካቲት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቅዳሜ ገበያ መስጊድ ፊት ለፊት ከሶላት ስግደት መልስ ወደ ቤታቸው በማምራት ላይ የነበሩት ሀጅ መሐመድ ዘይኑ ባልታወቁ የታጠቁ ግለሰቦች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።
በወቅቱ ወንጀለኞቹ የሟቹንና የሌሎች ግለሰቦችንም ስልክ ቀምተው መሰወራቸውን ተጎጂዎች ለፖሊስ አመልክተው ነበር።
ጥቆማውን ተቀብሎ ክትትል ሲያደርግ የቆየው ፖሊስ፣ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ተጠርጣሪው እዮብ ሞገስ አስቸ በማራኪ ክፍለ ከተማ ‘አየር ጤና’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርቶ አግኝቶታል።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ለመዋል ፍቃደኛ ባለመሆኑና ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት በመፍጠሩ እርምጃ የተወሰደበት መሆኑን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
ፖሊስ ባደረገው ማጣራትና ስልካቸውን የተቀሙ ግለሰቦች በሰጡት ቃል መሠረት፣ ወንጀል ፈጻሚውን መለየት እንደሚችሉ በገለጹት መሠረት በተደረገ የማረጋገጥ ሥራ ግድያውን የፈጸመውና ስልክ ሲቀማ የነበረው ግለሰብ እዮብ ሞገስ አስቸ መሆኑ ተረጋግጧል።
ኮማንደር አንተነህ አክለውም ከሟቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸውና አብረውት ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሌሎች ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የምርመራ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ማህበረሰቡ ለጸጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል የ ጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ ጥሪ አቅርበዋል።
እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን መነሻ በማድረግ ግጭቶችን ለማባባስ በሚሞክሩ ማናቸውም አካላት ላይ ፖሊስ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።
በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ ተፈጽሞ የነበረው የግድያ ወንጀል ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በጎንደር ከተማ ቀበሌ 02 ልዩ ስሙ ‘ይሳሱ ፔንሲዮን’ ውስጥ ተከስቶ በነበረው የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማው ፖሊስ ገልጿል።
እንደ ፖሊስ መረጃ፣ ጥር 09/2018 ዓ.ም በፔንሲዮኑ ውስጥ የአንድ ሰው አስከሬን በአልጋ ስር ተገኝቶ ነበር።
ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ምርመራ ሟች እና ተጠርጣሪው ሙሉቀን ተስፋ በጥር 07/2018 ዓ.ም አልጋውን በጋራ ተከራይተው የነበረ ቢሆንም ተጠርጣሪው ወንጀሉን ፈጽሞ እንደጠፋ ታውቋል።
ተጠርጣሪውን ለመያዝ የወጣውን የመያዣ ትዕዛዝ መነሻ በማድረግ፤ የፌደራል ፖሊስ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ እና የጎንደር ከተማ ፖሊስ በቴክኖሎጂ የታገዘ የጋራ ቅንጅት ስራ ሰርተዋል።
በዚህም መሰረት ተጠርጣሪው ሙሉቀን ተስፋ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው እየተካሄደ መሆኑን የጎንደር ከተማ ፖሊስ ገልጿል።




