በሰሜን ሸዋ ዞን የሠላምን አማራጭ የተከተሉ ታጣቂዎች ለሠራዊቱ እጅ ሰጡ።
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን አራጢ እና መርገጭ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲንቀሳቀሰ የነበረው የህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድን ወይንም ራሱን የባልከው ከበደ ሻለቃ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ወደ ሰሜን ሽዋ ዞን ደራ ወረዳ በመሄድ ለመከላከያ ሠራዊት ከነሙሉ ትጥቃቸው እጅ እንደሰጡ የ6ኛ ዕዝ ጋሻ ክፍለ ጦር መገናኛ ሃላፊ ሻለቃ ወጋየሁ በቀለ ተናግረዋል።
ቡድኑ ከዚህ በፊት እጅ ከሰጡት ፍቃዱ በላይ ክፍለ ጦር ብለው የሚጠሩት አባል እደነበሩና ተገንጥለው የጥፋት ሴራቸውን ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የቆዩ መሆናቸውን ሻለቃ ወጋየሁ በቀለ ገልፀዋል።
እጅ ከሰጡት የህገ-ወጥ ታጣቂው ቡድን አመራር መካከል ሻለቃ መሪ ብሎ ራሱን የሠየመው ባልከው ከበደ፤ የህገወጥነት መጨረሻው መበታተንና የሃገርን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ተላላኪ ከመሆን ውጭ ምንም ጥቅም እደሌለው በመረዳት ቡድኑን በመያዝ ለመከላከያ ሠራዊት እጅ በመሰጠት የሰላም አማራጭን መርጠናል ሲል ተናግሯል።
በአሁን ስዓት የህገ-ወጥ ታጣቂዎች የሠላምን አማራጭ በመጠቀም የበደሉትን ሃገርና ህዝብ ለመካስ በማሰብ ወደሰላም እጃቸውን በመዘርጋት በሰላማዊ መንገድ ለሠራዊቱ እጅ እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።



