አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ተከበረ
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ ” በሚል መሪ ቃል በዛሬው እለት በድምቀት አክብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ፣ የሴቶች ቀን ማርች 8 ሴቶች መብታቸውን ለማስከበርና በሁሉም ዘርፍ እኩል ተሳታፊ ለመሆን ያደረጉትን የዘመናት ትግል የሚያስታውስ ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል።
እናትነት እና የፖሊስነት ግዴታን አጣምሮ መያዝ እጅግ ፈታኝ ቢሆንም፣ የሀገራችን ሴት የፖሊስ አባላት ይህንን ድርብ ኃላፊነት በከፍተኛ ጽናትና ወኔ እየተወጡት ይገኛሉ ።
ይህ ቀን ለሴት የፖሊስ አባላት ደግሞ ትርጉሙ ላቅ ያለ ነው ያሉት አዛዡ ፖሊስነት ፅናት ፣ቁርጠኝነትና ፍትሃዊነትን የሚጠይቅ ሙያ እንደመሆኑ ሴት አባላት እነዚህን እሴቶች በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ ብለዋል።
በክልላችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት በተደረጉ ኦፕሬሽኖች ላይ እስከ ህይወት መሰዋትነት ድረስ በመክፈል ለሀገር ያላቸውን ፍቅር በተግባር አሳይተዋል።
ምንም እንኳን ሁሉም ሴት ሰራተኞች ለሀገር ግንባታ የየራሳቸው አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ሌሎች ሰራተኞች በቢሮ ወይም በተመደበላቸው የሙያ ዘርፍ አገልግሎት ሲሰጡ፣ ሴት ፖሊሶች ግን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ሲሉ ህይወታቸውን እስከመስጠት የሚደርስ አደገኛ ግዳጅ ውስጥ ይገባሉ።
እነዚህ እናቶች ለልጆቼ የምትመች ሀገር መኖር አለባት በሚል እምነት፣ ዩኒፎርማቸውን ለብሰው በድንበር አካባቢዎች በጽናት ህግን እያስከበሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው እናትነት የሚሰጣቸውን የርህራሄና የጥንቃቄ ባህሪ ከፖሊስነት ቁርጠኝነት ጋር በማጣመር የሀገርን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እያስጠበቁ ይገኛሉ ብለዋል።
አዛዡ አክለውም፣ ሴት አባላትን ማብቃትና በሃላፊነት ቦታዎች ላይ ማምጣት የተቋሙ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየሁ ታደሰ፣ የሴቶች ቀን (ማርች
ሴቶች ለሀገራቸውና ለማህበረሰባቸው መብት መከበር ዋጋ የከፈሉበትን ታሪክ የምናስብበት መሆኑን ገልጸዋል።
መብትና ሰላምን ማስከበር ከቤት ይጀምራል ያሉት ኃላፊው፣ ሴት የፖሊስ አባላት የቤት ውስጥ ኃላፊነታቸውን ተቋቁመው በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ ከወንዶች ባልተናነሰ ብቃት ግዳጃቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሴት የፖሊስ አባላት በስራቸው ወቅት የሚያሳዩት የብረት ፅናት እና የህዝብን ችግር የመረዳት የርህራሄ ጥበብ ተቋሙ የህዝብ አመኔታን እንዲያገኝ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል ብለዋል።
የሴቶችና ህፃናት ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ዋና ኢንስፔክተር ትዕግስት አለምነው በበኩላቸው፣ ፖሊስነት ከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት የሚጠይቅ ሙያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴት አባላት በማናቸውም የአመራርነት ጥበብና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን በመላበስ ውጤታማ እየሆኑ መመጣታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በክልሉ የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በፅናት በመመከት ረገድ የሴት ፖሊሶች ሚና ታሪካዊ መሆኑን አብራርተዋል።
ውስብስብ በሆኑ የህግ ማስከበር ስራዎች ላይ ያላቸውን ሙያዊ ስነ-ምግባርና ትዕግስት በመጠቀም ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ዋና ኢንስፔክተር ትግዕስት አለምነው ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሴት ፖሊሶች ሚና ከቤት ውስጥ የቤተሰብ መሪነት አልፎ የሀገሪቱን ሰላምና ዳር ድንበር ለማስከበር በሚደረገው ጉዞ ፍቅራቸውን ለልጆቻቸው ህይወታቸውን ደግሞ ለሀገራቸው አሳልፈው በመስጠት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሀገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅና የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ለረጅም ቀናትና ወራት ከልጆቻቸውና ከቤተሰባቸው ርቀው በበረሃና በድንበር አካባቢዎች ግዳጃቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም የውይይቱ ተሳታፊዎች አክለዋል።
ሴት የፖሊስ አባላት በክልሉ በሚሰጡ ማናቸውም የግዳጅ ስምሪቶች ላይ ከወንዶች ባልተናነሰ ብቃትና ወኔ እየተሳተፉ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።
ሴት ፖሊሶች ከአካላዊ ብቃት በተጨማሪ በስነ-ልቦና የታነጹና በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ውሳኔ የመስጠት ብቃት ያላቸው ናቸው።
እንደ መደበኛው የመንግስት ሰራተኛ በ8 ሰዓት ስራ የማይወሰኑ በሌሊትም ይሁን በበዓላት ቀናት ለህዝብ ደህንነት ሲሉ በንቃት የሚሰሩ ናቸው።
ሴት የፖሊስ አባላት ለክልሉና ለሀገሪቱ ሰላም እያበረከቱት ያለውን ታላቅ ተጋድሎ ሁሌም የሚዘክር ነው ብለዋል።
ተቋሙ የሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት በማንኛውም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በስኬት ለመወጣት ቃል የገቡት ተወያዮቹ ቀጣይ የሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
ሴት የፖሊስ አባላት በተሰማሩበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ እያሳዩት ያለው ጀግንነትና የህግ ማስከበር ፅናት ለሌሎች ሴቶችም አርአያ የሚሆን መሆኑ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም ለሀገር ሰላም ሲሉ የህይወት መሰዋትነት እየከፈሉ፤ የኢትዮጵያን ሰላም ለሚጠብቁ በየበርሃውና በየምሽጉ ለሚገኙ የምንጊዜም ጀግኖች ሴት ፖሊሶች በበዓሉ ላይ ልዩ ምስጋና ቀርቦላቸዋል ።











