ፖሊስ ከወጣቱና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገለጠ።

ፖሊስ ከወጣቱና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገለጠ።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ከወጣቶችና ከጠቅላላው ማኅበረሰብ ጋር የተቀናጀ የጸጥታ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን አስታውቋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ እንደገለጹት ፖሊስ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከክልልና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል።

በተለይም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ የጸጥታ ከባቢ ተፈጥሯል ብለዋል።

ተቋሙ የሰላም ግንባታ ሥራው ስኬታማ እንዲኾን ከወጣቱ ጋር ያለውን ግንኙነትና መግባባት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠሉን ኮማንደሩ ጠቁመዋል።

ወጣቱ የሰላም ዘብና አምባሳደር ነው ያሉት አዛዡ ለሚፈጠሩ ማናቸውም የጸጥታ ስጋቶች ወጣቱ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመመካከርና መረጃ በመለዋወጥ ረገድ የማይተካ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪ ወጣቶች በበኩላቸው ሰላምን የማጽናት ሥራው የጸጥታ አካላት ብቻ ሳይኾን የጠቅላላው ኅብረተሰብ ኃላፊነት መኾኑን አንስተዋል።

ፖሊስና ማኅበረሰቡ ተቀራርበውና ተግባብተው መሥራታቸው ለጸጥታ ሥራው መሳካት መሠረት መኾኑን ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

ማናቸውም ጸረ-ሰላም ተግባራት ከመከሰታቸው በፊት በሕዝብ ጥቆማና በፖሊስ ፈጣን እርምጃ እንዲታረሙ የሁለቱ አካላት ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ከእጅ የወጣን ሰላም ለመመለስ የሚከፈለው ዋጋ ከፍተኛ በመኾኑ ወጣቱና ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመኾን ሰላምን የመጠበቅ ሥራን ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ሲሉ ነዋሪዎቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ወገንተኝነትና አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር ማንኛውንም የሰላም ዕንቅፋት በጋራ ለመከላከል ዝግጁ መኾኑን አረጋግጧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top