በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ህገ-ወጥ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ዋለ።
መነሻውን ከጎንደር ከተማ አድርጎ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በህገ-ወጥ መንገድ ሊሰራጭ የነበረ 19 ሺህ 6 መቶ ሊትር ነዳጅ በህብረተሰቡ ጥቆማና በጸጥታ ኃይሉ የነቃ ክትትል በማይፀብሬ ፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ህገ-ወጥ ነዳጁን በ98 በርሚል ጭነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶስት የጭነት ተሽከርካሪዎችም
የሰሌዳ ቁጥር AA 07895 (FSR የጭነት መኪና)
የሰሌዳ ቁጥር AA 51915 (FSR የጭነት መኪና)
የሰሌዳ ቁጥር AA 33692 (ISUZU የጭነት መኪና) በማይፀብሬ ፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአጠቃላይ 98 በርሚል ወይም 19 ሺ 6 መቶ ሊትር ነዳጅ በህገ-ወጥ መንገድ ጭነው ሲጓዙ እንደነበር ተረጋግጧል።
በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ መደረጉን ተከትሎ እንዲህ ያሉ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
ድርጊቱ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያደናቅፍና ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርግ የኢኮኖሚ አሻጥር መሆኑን ያመላክታል።
ነዳጁን መውረስ ብቻ ሳይሆን ይህንን ነዳጅ የቀዱና ለህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች አሳልፈው የሰጡ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችን የመለየት ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ፖሊስ አረጋግጧል።
ህገ-ወጥ ድርጊቱ ከምንጩ ካልተገታ በስተቀር የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል በመገንዘብ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ተሳታፊዎች ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁሟል።
ለዚህ ስኬታማ ኦፕሬሽን የህብረተሰቡ ጥቆማና ያሳየው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ፖሊስ ጠቁሟል።
የአካባቢው ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ከህገ-ወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ለመጠበቅ እያደረጉት ያለው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ፖሊስ ገልጾ ለተደረገው ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።
የጸጥታ ኃይሉ እንዲህ አይነት የሀገርን ሀብት የሚያባክኑ ተግባራትን ለመከላከልና ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን በቀጣይም ህብረተሰቡ የተለመደ ድጋፉንና ጥቆማውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።



