በቡልጋ ከተማ የፖሊስና የማህበረሰብ ቅንጅት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ትልቅ ሚና መጫወቱ ተገለጸ።

በቡልጋ ከተማ የፖሊስና የማህበረሰብ ቅንጅት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ትልቅ ሚና መጫወቱ ተገለጸ።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ሳይበግሯት በሰሜን ሸዋ ዞን የቡልጋ ከተማን ሰላም አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስቀጠል መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የቡልጋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኮማንደር ወርቅውሃ ጉልላት እንደገለጹት ለዚህ ስኬት ዋነኛው ምክንያት በፖሊስና በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠረው ጠንካራ የጋራ ጥረት ነው ብለዋል።

ኮማንደሯ አያይዘውም የከተማዋን ሰላም ለማጽናት ከሌሎች የፀጥታ አካላትና ከህዝቡ ጋር በተደረገ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግና ህዝቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማቀናጀት ቀደም ሲል ዋነኛ ስጋት የነበረውን የግድያ ወንጀል በተያዘው በጀት ዓመት በከፍተኛ መጠን መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

የእገታ፣ የዝርፊያ እና የሰርጎ ገብነት ወንጀሎች ለከተማዋ ከፍተኛ ስጋት የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን አዛዧ ገልጸዋል።

በወንጀል ምርመራ ረገድ የህዝቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኮማንደር ወርቅውሃ ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ መዝገቦች ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

ከነዚህም መካከል 16 የሚሆኑ መዝገቦች በተፋጠነ የምርመራ ዘዴ ተጣርተው ለፍርድ እንዲበቁ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው የሪፎርም ስራ ወደ ተግባር መለወጡን ጠቅሰው ለሙያው ክብርና ፍቅር ያለው ለህዝብ አገልግሎት ዝግጁ የሆነ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት ማገዙን ተናግረዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ እየተገነባ የሚገኘው “የጀግኖች ማዕከል” የክልሉን ፖሊስ ተስፋ የሚያለመልም እና የተቋሙን ከፍታ የሚያሳይ በመሆኑ የቡልጋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና ከስምምነት ላይ መድረ ኮማንደር ወርቅውሃ ጉልላት አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top