ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገለጸ።

የፊታችን የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀምረው 7ኛው ሀገራዊ የምርጫ ምዝገባ ሂደት ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስፈላጊውን ዝግጅት በላቀ ደረጃ ማጠናቀቁን ይገልጻል።

ህብረተሰቡ ያለምንም የጸጥታ ስጋት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ የመመዝገብ መብቱን እንዲጠቀም ለማስቻል የጸጥታ ኃይላችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በከፍተኛ ተጠንቀቅና ዝግጅት ላይ ይገኛል።

ዜጎች በነፃነትና በሰላም ውሳኔያቸውን የሚሰጡበት ምህዳር እንዲፈጠር የጸጥታ አካሉ የሰላም ዘብ ሆኖ የመቆም ጽኑ ቁርጠኝነት አለው።

የሀገርን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የክልሉ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ስምሪት ስራዎችን አጠናቋል። ከወትሮው በተለየ መልኩ ከህብረተሰቡ ጋር የቅርብ ትስስር በመፍጠርና የተለያዩ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አደረጃጀቶችን በንቃት በማሳተፍ ሰላምን የማስከበር ስራው በህዝብ ባለቤትነት እንዲመራ እየተደረገ ይገኛል።

ተቋማችን የጀመረው ዘመናዊ የሪፎርም ስራ እና የዲጂታላይዜሽን ስርአት ለዚህ ምርጫ ሂደት ስኬታማነት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።

የመረጃ ልውውጥን በማዘመን የሰው ኃይል ስምሪትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እና የአሰራር ግልጽነትን በመፍጠር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ በሰለጠነና በተደራጀ መልኩ እንዲከናወን ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

ከምርጫ ምዝገባው ሂደት ባሻገር ለዋናው የምርጫ ዕለትም የክልሉ ፖሊስ በታማኝነት፣ በገለልተኝነት እና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን።

ማንኛውንም የሰላም መደፍረስ ሙከራ አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ኃይላችን የማይናወጥ አቋም አለው።

በመጨረሻም መላው የክልላችን ህዝብ ለምርጫ ምዝገባው ሰላማዊነት ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የሰላም መረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሰረት ነው!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top