በጎንደር ከተማ ሶስት ሰዎችን የገደለውና ውንብድና የፈፀመው ግለሰብ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሸንበቂት አካባቢ ነዋሪዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለ እና ከባድ የውንብድና ወንጀል የፈፀመው ተከሳሽ ማሞ ካሴ፣ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ተከሳሹ ማሞ ካሴ ቀደም ሲል በመሬት ጉዳይ ምክንያት ከግለሰቦች ጋር የነበረውን ቂም መነሻ በማድረግ፣ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ አራት ተባባሪዎቹን በመያዝ በፈፀመው ጥቃት ወ/ሮ ወርቄ ተገኘ እና የ5 ዓመት ህፃን የሆነውን በሱፍቃድ ተገኘን በክላሽንኮቭ መሳሪያ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል።
ወ/ሮ የዝና ደርሶን በተደጋጋሚ በጥይት በመምታት ከባድ አካል ጉዳት ያደረሰባቸው ሲሆን፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው አልፏል።
አቶ አያሌው ማለደ የተባሉ የግል ተበዳይን በመኖሪያ ቤታቸው በመሄድ በጠመንጃ ሰደፍና በዱላ ጭንቅላታቸውን በመደብደብ፣ የራሳቸውን የግል መሳሪያ (ክላሽንኮቭ) ከ19 ጥይቶች ጋር (በገንዘብ 151,900 ብር የሚገመት) ዘርፏል።
ተበዳይ ሙሌ አያሌው ላይ ድብደባ በመፈፀም 30,000 (ሰላሳ ሺህ) ብር ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን መውሰዱ በችሎት ተረጋግጧል።
እንደ ኮማንደር አልማዝ ላቀው የጎንደር ከተማ ፖሊስ ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ ገለጻ ተከሳሹ ማሞ ካሴ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በጎንደር ከተማ አስተዳደር የ1ኛ ፖሊስ ጣቢያ ምርመራውን አጣርቶ እና መዝገቡን አደራጅቶ ለዞኑ ዐቃቤ ህግ ልኳል።
የዞኑ ዐቃቤ ህግም በከባድ የሰው መግደል፣ በመግደል ሙከራ እና በከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም የተያዘውን የጦር መሳሪያ (ኤግዚቢት) መርምሮ ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ወንጀለኛው እንዲማርበትና ሌሎች መሰል ድርጊት እንዳይፈፅሙ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን በማሰብ፣ የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
ከወንጀለኛው ጋር በጥቃቱ የተሳተፉና ያልተያዙ ሌሎች አራት ግብረ አበሮችን የመከታተል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር አልማዝ ላቀው የጎንደር ከተማ ፖሊስ ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ አስታውቀዋል።

