የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ዙር የማዕረግ ሽግግር ሰልጣኞች ደማቅ አቀባበል አደረገ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተቋሙ እየተተገበረ ያለውን መጠነ ሰፊ ሪፎርም ተከትሎ ከኢንስፔክተር ወደ ዋና ኢንስፔክተርነት ማዕረግ ለሚሸጋገሩ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች ደማቅ አቀባበል አድርጓል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያካሄደ ያለውን ተቋማዊ ሪፎርም መነሻ በማድረግ የተዘጋጀው ይህ ስልጠና ሰልጣኞቹ አስቀድሞ የተዘጋጀውን የብቃት መመዘኛ ፈተና በስኬት ያለፉ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የዝግጅት ክፍል አረጋግጧል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ በሰልጣኞች አቀባበል ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የፖሊስ ሰራዊቱን ሪፎርም ለማስቀጠልና የሰው ኃይልን በዕውቀት ለማነጽ የሚሰራ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የማዕረግ እድገት በቆይታ ጊዜ ላይ ብቻ ተመስርቶ ይሰጥ የነበረ መሆኑን አስታውሰው አሁን ግን ለዕውቀትና ለክህሎት ቅድሚያ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱን አብራርተዋል።
አንድ አመራር ወደ ቀጣዩ ከፍተኛ ማዕረግ ሲሸጋገር ከማዕረጉ ጋር የሚመጥን የላቀ ዕውቀትና የአመራር ጥበብ ሊኖረው እንደሚገባም
አሳስበዋል።
የማዕረግ ሽግግሩ ስልጠና ዋና ግብ አመራሩ የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ስራውን በዘመናዊ ዕውቀትና በሰለጠነ መንገድ እንዲመራ ማስቻል እንደሆነ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ በበኩላቸው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም የቀደሙ አሰልቺና ባህላዊ አሰራሮችን በመስበር ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ አክለውም የተጣለባቸውን ከፍተኛ የህዝብ አደራ ለመወጣትና የሚሰጠውን ስልጠና በንቃት በመከታተል አቅማቸውን ለማሳደግ ሙሉ ዝግጁነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።






