በምሥራቅ ዕዝ ኦፕሬሽን ከ200 በላይ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን አባላት ተደመሰሱ

በምሥራቅ ዕዝ ኦፕሬሽን ከ200 በላይ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን አባላት ተደመሰሱ

በምሥራቅ ዕዝ ሥር የሚገኙ የሰራዊት ክፍሎች ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት ባከናወኑት የተጠና ኦፕሬሽን ከ200 በላይ የህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድን አባላት መደምሰሳቸውንና በርካታ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዕዙ አስታወቀ።

ኦፕሬሽኑ በሰሜንና ምዕራብ ጎጃም፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በማዕከላዊ ጎንደር አዋሳኝ ቀጣናዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም 135 ታጣቂዎች ሲደመሰሱ፣ 68 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን ያስታወቀው የምስራቅ ዕዝ፤ 46 ኤኬኤም (ክላሽንኮቭ)፣ 43 የቃታ መሣሪያዎች፣ አንድ ፒኬኤም መትረየስ፣ አንድ ስናይፐር፣ 5 ቦምቦችና ልዩ ልዩ ተተኳሾችም ተይዘዋል።

ሠራዊቱ በተለያዩ ግንባሮች በወሰደው ስምሪት በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሽንፈት ማድረሱን ዕዙ ገልጿል።

በዳንግላ ዙሪያ (ጭሮ፣ ፋግታ፣ ደብረ ወርቅ፣ ድማማ አንገረብ፣ በዋዝ እና ደብረ ዘይት)፦ 50 ጽንፈኞች ሲገደሉ፣ 39 ቆስለዋል፤

በሰከላ ወረዳ (ሱርባ ቀበሌ)፦ 47 ጽንፈኞች ተደምስሰው፣ 14 ቆስለዋል፤

በማዕከላዊ ጎንደር (አለፋ ወረዳ ሻውራ ከተማ አቅራቢያ)፦ 38 የጥፋት ኃይሎች ሲደመሰሱ፣ 15 መቁሰላቸውን የምስራቅ ዕዝ አክሎ አስታውቋል።

ከየካቲት 13/2018 ዓ.ም ወዲህ በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ፣ የቡድኑ ቁልፍ አመራሮች መደምሰሳቸው ተረጋግጧል።

ከእነዚህም መካከል፦

• ንብረት መላኩ (የሻለቃ አዛዥ)

• ብርሃኑ በላይነህ (የሻለቃ ዘመቻ)

• አለማየሁ ጌቴ (የሻለቃ መሪ)

• አስቻለው በውሉ (የክፍለ ጦር ሎጀስቲክስ)

• ምህረቴ አየለ (የሻለቃ ዘመቻ)

• ብርቁ ደሴ (የክፍለ ጦር ዘመቻ)

• ነጋ ባቡቾ (የኮር ፖለቲካ ኃላፊ)

• ዘሪሁን (ጊዮርጊስ) (የክፍለ ጦር ዘመቻ ኃላፊ) ይገኙበታል።

ቡድኑ ከውጭ የተሰጠውን ተተኳሽ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማተራመስና ሰርጎ ለመግባት ያደረገው ሙከራ በአባድራ አቅጣጫ በደረሰበት ምት መክሸፉን ዕዙ ጠቁሟል።

የክልሉ የጸጥታ ኃይልና ሕዝቡ ባደረጉት ድጋፍ፣ ታጣቂው ቡድን መደበቂያ በማጣት እርስ በርስ እንዲጋጭና እጁን እንዲሰጥ መገደዱም ተገልጿል።

ምሥራቅ ዕዝ አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ሕግ የማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሚ አረጋግጧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top