“የአድዋ ድል ለዘላቂ ሰላምና አንድነት!”

“የአድዋ ድል ለዘላቂ ሰላምና አንድነት!”

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ 130ኛውን የአድዋ ድል በዓል በፓናል ውይይት አከበረ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ 130ኛውን የአድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ቃል ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በፓናል ውይይት አክብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የበታችነት ስሜት ተወግዶ የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና የአፍሪካውያን የነፃነት ፋና የበራበት ታላቅ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።

ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ አክለውም የአድዋን ድል ስናከብር የአባቶቻችንን የአንድነት መንፈስ በመላበስ መሆን አለበት።

ክልሉ የገጠመውን የፀጥታ ችግር ለመፍታትና የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የአድዋ ድል ትልቅ ስንቅ መሆኑን ጠቁመው፣ የዚህ ትውልድ ታሪክ የሀገሪቱን የእድገት ጉዞ ማሳለጥ መሆን እንዳለበት ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ አሳስበዋል።

የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበኩላቸው፣ ከትናንት አኩሪ ታሪክ ተሞክሮ በመውሰድ ለዛሬ ስንቅና ለነገ ግንባታ መጠቀም የትውልዱ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገርን ክብርና ሰላም የሚነኩ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመመከት የአድዋን ታሪክ መድገም እንደሚገባም አክለዋል።

በውይይቱ ላይ ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል የዘመኑን ድል ማብሰር እንደሚገባ በአጽንኦት ተገልጿል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዓሉን ስናከብር ለሀገር ሰላም ውድ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ የፀጥታ አባላትን በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል።

የአባቶችን አይበገሬነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ፈለግ በመከተል በአላማ መጽናት እንደሚገባ አክለው ያስታወቁት የውይይቱ ተሳታፊዎች በአንድነትና በቁርጠኝነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የፓናል ውይይቱ ታሪካዊውን የአድዋ ድል ከአሁናዊ የሀገሪቱ የሰላምና የልማት እንቅስቃሴዎች ጋር በማዛመድ የጋራ ግንዛቤ የተያዘበት መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top