አድዋ የጀግንነት ማህደርና የኢትዮጵያዊነት ፅናት!
ነገ የሚከበረውን የ130ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ የአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለጸጥታ ኃይሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
በመግለጫውም አድዋ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ የማይደፈሩ የዓለም ድንቅ ህዝቦች መሆናቸውን የተመሰከረበት የታሪክ አሻራ መሆኑ አመልክቷል።
የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ዘመናዊ ትጥቅ በታጠቀው ወራሪ ኃይል ላይ ድልን የተቀዳጁት በሀገር ፍቅር ስሜት፣ በወንድማማችነትና በማይበገር ፅናት መሆኑን የጠቀሰው ዋና ጠቅላይ መምሪያው የዛሬው ትውልድም ይህንን የታሪክ አደራ በመረከብ የሀገሩን ሉዓላዊነትና ሰላም የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት አሳስቧል።
ኢትዮጵያ ሁሌም ለጠላቶቿ የማትደፈር የእግር እሳት ናት፤ ይህንንም በተግባር ለማረጋገጥ የፖሊስ ሠራዊታችን ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት ሁሉ የሉዓላዊነቷ ደፋሪዎችን አሳፍራ የመለሰች የጀግኖች ምድር ናት።
አሁንም ቢሆን ሀገራችንን ለማፍረስና ሰላሟን ለማደፍረስ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች፣ የአድዋን ታሪክ ዳግም እንዲያነቡና ከኢትዮጵያውያን ፅናት እንዲማሩ ጥሪ አቅርቧል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአባቶቹን ጀግንነት በመላበስ፣ የህዝብን ደህንነትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቀንና ሌሊት በፅናት እየሰራ ይገኛል ብሏል ዋና ጠቅላይ መምሪያው።
ሠራዊቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለመጠበቅ የማይተካ ህይወቱን እንደ አባቶቹ በገጸ-በረከትነት እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቁሟል።
ፖሊስ ከህዝብ የወጣና ለህዝብ የቆመ በመሆኑ፣ ማንኛውንም የጥፋት ኃይል በመመከት ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝም ዋና ጠቅላይ መምሪያው አረጋግጧል።
በመጨረሻም፣ መላው የፖሊስ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ህዝብ በዓሉን በሰላምና በታላቅ ኩራት እንዲያከብር
መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!


