በመግደል ሙከራ ተከስሶ የተሰወረው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ

በመግደል ሙከራ ተከስሶ የተሰወረው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ

በቀድሞ ፍቅረኛው ላይ የመግደል ሙከራ ወንጀል ፈጽሞ ለወራት ተሰውሮ የቆየው ተጠርጣሪ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ተይዞ ለባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ መሰጠቱ ታወቀ።

ተጠርጣሪው ኢዮብ (ናትናኤል) ጫኔ በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ በሆነችው ወጣት ትዕግስት አየነው ላይ ከዚህ ቀደም የግድያ ሙከራ ወንጀል ፈጽሞ የነበረ ሲሆን፣ ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ተሰውሮ ቆይቷል።

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ግለሰቡ በሌለበት ጉዳዩን መርምሮ በህዳር 19 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ በ8 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

ተከሳሹ ከባህር ዳር በመሸሽ በአዲስ አበባ ከተማ ተደብቆ መቆየቱን የገለጸው ፖሊስ፣ ውሳኔ የተላለፈበትን የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ መሰረት በማድረግ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እንደገለጸው የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 12:00 ሰዓት ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ገርጂ ዱባይ ሞል አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ፣ ለተፈለገበት ለባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ተላልፎ ተሰጥቷል።

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ምስጋና ያቀረበው የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ይህ እርምጃ ወንጀል ፈጽሞ ማምለጥም ሆነ ተሰውሮ መኖር እንደማይቻል ያሳየ ሲሆን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሌሎች ክልል ፖሊስ ጋር ያለው ቅንጅት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብሏል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top