የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ በይፋ ተጀመረ።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የክልሉ ፖሊስ ጀግኖች ማዕከል የቁፋሮ ስራ በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።
የግንባታ ስራውን የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ እና የዞኑ ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በተገኙበት ተጀምሯል።
ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ በወቅቱ እንደገለጹት፣ የማዕከሉ መገንባት በሪፎርም ስራዎች ውስጥ የታቀደ ሲሆን ለቆሰሉና አካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰራዊቶች ልዩ ልዩ ጥቅሞችን ይሰጣል ብለዋል።
ከህክምና በኋላ የሰራዊት አባላት የተሟላ የማገገሚያ ክትትል እንዲያገኙ ማስቻል፤
ጉዳት የደረሰባቸው አባላት ልዩ ልዩ ሙያዎች ሰልጥነው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ፤
እንዲሁም ተቋሙን ለጥናትና ምርምር ስራዎች አገልግሎት እንዲውል ማድረግ የሚሉ ሶስት ዋና ዋና ጥቅሞችን ይሰጣል ሲሉ ረዳት ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ አስታውቀዋል።
ለግንባታው የሚውለው የገንዘብ ምንጭ በዋናነት ከሰራዊቱ አባላት መዋጮ የተገኘ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ከጻፉት የመጽሐፍ ሽያጭ ለዚሁ ማዕከል ግንባታ እንዲውል መወሰኑ ተገልጿል።
ለዚህም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) መላው የአማራ ክልል ፖሊስ ሰራዊት ምስጋና ችሯቸዋል።
የግንባታ ስራውን የተረከበው ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ግንባታውን በጥራት አከናውኖ በ6 ወራት ውስጥ እንደሚያስረክብ ቃል ገብቷል።







