በፖሊስ ስም የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራትንና የሰነድ ማጭበርበርን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የዲጂታል መታወቂያ አሰራር ተግባራዊ መሆን ጀመረ።
መታወቂያው በውስጡ በያዘው የ QR Code ቴክኖሎጂ አማካኝነት የማንኛውንም የፖሊስ አባል ማንነት በሰከንዶች ውስጥ በታማኝነት ለማረጋገጥ ያስችላል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የፖሊስ አባላቱንና አመራሮቹን የስራ መታወቂያ ወደ ዲጂታል ስሪት በመቀየር፣ የተቋሙን አሰራር ለማዘመንና የጸጥታ ስራውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን አስታውቋል።
ይህ የዲጂታል መታወቂያ ዝግጅት ዋና ጠቅላይ መምሪያው ራሱን በቴክኖሎጂ ለማብቃት የጀመረው መጠነ ሰፊ የሪፎርም ስራ አካል መሆኑን ያመላክታል።
የአማራ ክልል ፖሊስ አባላትና አመራሮች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸው፣ በክልሉ ያለውን የጸጥታ መዋቅር ጥራት ከማሳደጉም በላይ፣ አባላቱ በኩራትና በራስ መተማመን ስራቸውን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል።
የክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ድጅታል መታወቂያ ስርዓት የደህንነት አገልግሎትን ወደ ዘመናዊነት በማሸጋገር ላይ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንዲሁም ለህዝብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት የሚያመላክት መሣሪያ ነው።
ይህ የዘመናዊነት ጉዞ ተቋሙ የወንጀል መከላከል አቅሙን ለማሳደግ የጀመረው ሰፊ የለውጥ ስራ ውጤት መሆኑን ያመላክታል።
አዲስ የዲጅታል መታወቂያው አሰራር ከዚህ ቀደም ይከተል የነበረውን ባህላዊ የመታወቂያ አሰጣጥ ወደ ዲጂታል የመረጃ ቋት በማሸጋገር ረገድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑንም ያመላክታል።
በወረቀት የሚዘጋጁ መታወቂያዎች በቀላሉ ሊሰረዙ፣ ሊደለዙ ወይም በሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጆች ሊቀዱ ይችላሉ። አዲሱ ዲጂታል መታወቂያ ግን በውስጡ QR Code እና የባዮሜትሪክ መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ፣ መታወቂያው የትክክለኛ የፖሊስ አባል መሆኑን በማንኛውም ቦታ በስካነር ወይም በሞባይል መተግበሪያ ወዲያውኑ ለማረጋገጥ ያስችላል።
ይህም የፖሊስን ስም በመጠቀም የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራትን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።
የዲጂታል መታወቂያው ከዋና ጠቅላይ መምሪያው ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ጋር የተገናኘ ነው። ይህም ማለት አንድ የፖሊስ አባል ከስራ ሲሰናበት፣ ሲቀነስ ወይም ሌላ አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወሰድበት፣ መታወቂያው የጊዜ ቆይታ (Expired date) ስላለው በሲስተም አማካኝነት ወዲያውኑ አገልግሎት የማይሰጥ (Inactive) እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ይህም መታወቂያውን ተመላሽ የማያደርጉ የፖሊስ አባላትን ቁጥጥር ቀላል ያደርገዋል።
መታወቂያው ስለ አባሉ ወይም አመራሩ መሰረታዊ መረጃ ብቻ ሳይሆን፣ የደመወዝ ደረጃን፣ የክህሎት ስልጠናዎችን፣ የደም አይነትን እና የቆይታ ዘመንን የያዘ ዲጂታል ፋይል እንዲኖር ያስችላል። ይህም ለሰው ኃይል አስተዳደር ስራ እጅግ ቀልጣፋ አሰራርን ይፈጥራል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መመሪያ ይህንን አሰራር ተግባራዊ ማድረጉ ተቋሙን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ወደጠበቀ የፖሊስ አገልግሎት እየተሸጋገረ መሆኑን ያመላክታል።
ማህበረሰቡ ፖሊስን ሲያገኝ የያዘው መታወቂያ ዘመናዊና ትክክለኛ መሆኑን ሲረዳ በተቋሙ ላይ ያለው እምነት ይጨምራል።
የፖሊስ አባላት ወደ ተለያዩ ተቋማት ወይም ክልሎች ለስራ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ማንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚፈጅባቸውን ጊዜ በእጅጉ ይቀንሰዋል።
በየጊዜው መታወቂያዎችን በማተም የሚባክነውን ወጪና ቢሮክራሲ በመቀነስ ረገድ ዲጂታል አሰራሩ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
የፖሊስ አባላትን መረጃ ወደ ዲጂታል መለወጥ ከ “EFP” መተግበሪያ ጋር ተዳምሮ የፖሊስን ስራ ሙሉ በሙሉ በዳታ ላይ የተመሰረተ ያደርገዋል።
ፖሊስ ራሱ በቴክኖሎጂ ሳይዘምን ወንጀልን በዘመናዊ መንገድ መከላከል እንደማይቻል የታመነበት በመሆኑ፣ ይህ ተግባር ለሌሎች የመንግስት ተቋማትም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው።



